የሶስተኛ ወገን መድን ፈንድ አገልግሎት አሰጣጥና የተሽከርካሪ መረጃ አያያዝ  በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ተደርጓል--የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት

198

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፡- የሶስተኛ ወገን መድን ፈንድ አገልግሎት አሰጣጥና የተሽከርካሪ መረጃ አያያዝ  በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በመደረጉ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ባሉበት ቦታ ሆነው ማግኘት እንደሚችሉ የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ ፡፡

የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በትራፊክ አደጋ መከላከል፣ መንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል ፡፡

በዚህም አገልግሎቱ ከክልልና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመቀናጀት በመንገድ ደህንነትና በትራፊክ አደጋ መከላከልና መንስኤ የግንዛቤ ማስጨበጫና የመንገድ ቁጥጥር ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል ፡፡

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለ 45 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በትራፊክ አደጋ የደረሰው የህይወት መጥፋት ካምናው አንጻር መቀነስ ቢያሳይም ቁጥሩ ግን አሁንም አሳሳቢ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 338 መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የሶስተኛ ወገን መድን ፈንድ አገልግሎት አሰጣጡና የተሽከርካሪ መረጃ አያያዙ ዘመናዊ ባለመሆኑ ከተገልጋይ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲነሳበት እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በማሰብ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ያበለጸጉትን ሶፍትዌር ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል ፡፡

አሽከርካሪዎች የመኪና ባለንብረቶችና የ3ኛ ወገን መድን ፈንድ ተጠቃሚዎች ወደ ተቋሙ መምጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው በዲጂታል መተግበሪያ የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ተገልጋዮችን ከእንግልት በመታደግ ፣ ጊዜአቸውን፣ ጉልበታቸውንና ወጪአቸውን ይቀንስላቸዋል ብለዋል ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከፌደራል ፓሊስ ጋር በመተባበርና ማዕከል ላይ የሚቀመጥ ሰርቨር በማዘጋጀት በሀገሪቱ አንድ ወጥ የሆነ የተሽከርካሪ መረጃ አያያዝ ስርአት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የትራፊክ አደጋ ከተከሰተ መቼ ፣ የት ፣እንዴትና  ምን ዓይነት ጉዳት እንደተከሰተ በፍጥነት መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደሚያስችል አስረድተዋል ፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም