በክልሉ አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በትኩረት እየሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

344

ጋምቤላ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከአኝዋሃ ዞን ከተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ዛሬ በጎግ ወረዳ በመከሩበት ወቅት ነው።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት የህዝቡን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በክልሉ በዘላቂነት ሰላም ለማስፈን መንግስት ለሚያደርገው ጥረት የማህበረሰቡ እገዛና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።

የህዝቡን ህይወት እንዲቀይሩ ታቅደው የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማሳካት በዋናነት በየአካባቢው የተረጋጋ ሰላም ማስፈን አስፈላጊ መሆኑንም ገልፀዋል።

በህዝቦች መካከል ያለውን ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር እሴቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በማፅናት ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መሳካት የህዝቡ ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ናቸው።


 

በተለይም ከለውጡ ወዲህ በክልሉ ሰፍኖ የቆየውን ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ አካላትን በህግ ለመጠየቅ መንግስት እያደረገ ላለው ጥረት ህዝቡ ተባባሪነቱን ማጠናከር እንደሚገባው ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት አሁን ላይ የጀመራቸውና ማህበረሰቡን ያሳተፉ የሰላም ግንባታ ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አሪያት ኡታንግ በሰጡት አስተያየት፤ የህዝቡን ሰላም በሚያውኩ አካላት ላይ መንግስት የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ ማጠናከር አለበት።

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግስት ለሚያደርገው ጥረት ሁሉ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።

ክልሉ ለሚያከናውናቸው የሰላም ግንባታ ስራዎች ስኬታማነት ከመንግስት ጎን በመሆን የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ኡቶው ኡዋር ናቸው።

መንግስት ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ አሁን እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የአመራር አባላትን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተዋቂ ግለሰቦች እና የህብረተሰቡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም