ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ምዝገባ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ለስኬቱ ተቋማት በቅንጅትና በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

284

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፡- ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም ለሀገራዊ የልማትና ለአገልግሎት አሰጣጥ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በተያዘለት እቅድ እንዲፈጸም ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ከመንግሥት ተቋማት ጋር በአጋርነት ያከናወናቸው ተግባራት አፈጻጸም ግምገማ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎችን ምዝገባ ማከናወኑም ተገልጿል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ዲጂታል መታወቂያ የሰዎችን ትክክለኛ ማንነት ለማረጋገጥና ለመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ነው።

መንግስት ዲጂታል መታወቂያ የሀገርን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎችን በተቀናጀ መንገድ ለመፈጸምና የፋይናንስ ስርዓቱን ደህንነት ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በማመን ወደ ስራ መግባቱንም ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ባንኮች ደንበኞቻቸውን አውቀው ብድር እንዲያቀርቡ፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲፋጠን ሚናው የላቀ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የመልካም አስተዳደር፣ የሠላምና የልማት እቅድ አፈጻጸምን ለማሻሻልም ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያሉት።


 

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሔ አርአያስላሴ፤ በመድረኩ የፕሮግራሙን የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የዲጂታል መታወቂያ ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ ከ50 ተቋማት ጋር ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማድረጋቸውን ገልጸው እስከ ሰኔ መጨረሻ 10 ሚሊዮን ለመመዝገብ መታቀዱን ተናግረዋል።

በቀን በአማካይ 8 ሺህ  የመታወቂያ  የማንነት ማረጋገጥ ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ለማሳካትና የመንግሥት ሠራተኞችን ትክክለኛ ማንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የትራንስፖርትና መሰል አገልግሎቶችን በተደራጀና ከሀገራዊ ግቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለመፈጸም አጋዥ እንደሆነ አንስተዋል።


 

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት መስቀሌ፤ በሚኒስቴሩ ቅርንጫፎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የሀገር ገቢን ለማሳደግና ትክክለኛ የታክስ አከፋፈል ስርዓትን ለመዘርጋት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ለአብነትም የቲን ቁጥር ለማውጣት የሚመጡ ደንበኞች በመጀመሪያ የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመው ተጨማሪ የመመዝገቢያ መሳሪያዎች እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።


 

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬ ህይወት ታምሩ፤ ደንበኞችን ከዲጂታል መታወቂያ ጋር ለማስተሳሰር እንዲሁም መታወቂያውን በቴሌ ብር ሱፐር አፕ የሚያገኙበት አሰራር መጀመሩን ተናግረዋል።

በኩባንያው በኩል ህብረተሰቡን የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እንዲያደርግ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው በአምስት ወራት ውስጥ እስከ አምስት ሚሊዮን ደንበኞችን ለመመዝገብ ግብ መያዙን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ ባንኮችን ወክለው የቀረቡ ተሳታፊ በበኩላቸው የተወሰኑ ባንኮች ደንበኞቻቸውን በትክክል አውቀው ተገቢውን የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እያካሄዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ምዝገባውን ለማስፋት 6 ሺህ የመመዝገቢያ መሳሪያዎች ግዥ ለመፈጸም ሂደቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ጸሐይ ጳውሎስ እንዳሉት እስከ 2018 መጨረሻ 90 ሚሊዮን ህዝብ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እንዲያከናውን ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

ለስኬቱም የምዝገባ ጣቢያዎችን በየተቋሙ ማደራጀት፣ የቴክኖሎጂ ስርዓቶችን ማስተሳሰር፣ የመመዝገቢያ መሳሪያዎችን ማሟላት እንዲሁም የተግባቦት ስራን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ነጥቦች በሰጡት ምላሽ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራምን ለማሳካት ሰፊ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ ከምዝገባ ጎን ለጎን የሀብት ማሰባሰብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ዓመታዊ ግቡን በቀሪ ወራት ለማሳካትም ተቋማዊ ቅንጅት ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይ ዓመት ወደ ሙሉ የትግበራ ምዕራፍ ለመግባት ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ አንስተዋል።

የምዝገባ መሳሪያዎችን ግዥ ማፋጠን፣ የተግባቦትና የግንዛቤ ስራዎችን ማስፋፋት የሁሉም ተቋማት ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው የፋይናንስ ተቋማትና ቴሌኮም በቀዳሚነት ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም