የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማሳደግ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አሰራር መዘርጋት ይገባል

66

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማሳደግ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አሰራር መዘርጋት የሚገባ መሆኑን የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አስታወቀ።    

ኢትዮጵያ ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገች ነው።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ባንኮችን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ከማድረግ ጀምሮ የካፒታል ገበያና የሰነድ ሙዓለ ነዋይ አሰራር ተጠቃሽ ነው።  

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርባ በመጠባበቅ ላይ ስትሆን የአፍሪካ አህጉራዊ  ነጻ ንግድ ቀጣናን ጨምሮ የተለያዩ አህጉራዊ የንግድ ሥምምነቶችን ገቢራዊ ለማድረግም ሰፊ እንቅስቃሴ በማደረግ ላይ ትገኛለች።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ አጎናፍር፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ እየተደረገ ያለው ጥረት ወቅታዊና የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አሰራር ስርአት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድም ኦዲተሮች በሂሳብ ባለሙያዎች የሚዘጋጀው የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማረጋገጥ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ቦርድ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኦዲት ሥርዓትን ለማዘመን በተዘጋጀው መመሪያ ላይ ለኦዲተሮች የአቅም ግንባታ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በአህጉር ደረጃም ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ አካውንትስ ፌደሬሽን አባል መሆኗን ገልጸው ፈደሬሽኑ በአፍሪካ ተቀራራቢ የፋይናንስ የኦዲት ሥርዓት እንዲኖር ያወጣው መመሪያ ላይ ግንዛቤ ጨብጠው ተግባራዊ እንዲያደርጉትም አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ 200 የሚሆኑ የኦዲት ድርጅቶች በቦርዱ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆኑ ድርጅቶቹ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

የኦዲት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአሰራር ስርአትም የተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል። 

 

 

 

    

 

  

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም