በኢትዮጵያ ለአካባቢ ተስማሚ የኢንዱስትሪ ስርዓትን በመገንባት ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል-ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለአካባቢ ተስማሚ የኢንዱስትሪ ስርዓትን በመገንባት ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል-ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ለአካባቢ ምቹና ተስማሚ የኢንዱስትሪ ስርዓትን በመገንባት በዘርፉ ቀጣይነትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ በሆነ መንገድ ዘላቂና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያግዝ ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ለማ ፕሮጀክቱ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የሚደረጉ የምርት እንቅስቃሴዎች አካባቢን በማይጎዳ መልኩ እንዲከናወኑ የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመንግስትና በልማት አጋር ድርጅቶች የተቀረጸው ይህ ፕሮጀክት አምራቾች በዘላቂነት በአገር ውስጥና በውጭ ተወዳዳሪ ሆነው ምርታቸውን እንዲያቀርቡ የሚያበረታታ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
አምራቾች የምርት ሂደታቸው በአካባቢ ላይ ተጽእኖ እንዳያደርስ የተረፈ ምርት አጠቃቀምና የኬሚካል አስተዳደርና አያያዝ ላይ ያላቸውን አቅም ለማሳደግ ይርዳል ብለዋል።
ለአምስት ዓመታት በሚተገበረው ፕሮጀክት በጨርቃጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለምርት ጥቅም የሚውሉ ኬሚካልና ፍሳሾችን በማጣራት መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉበት አሰራር መኖሩንም አክለዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የጋራ የፍሳሽ ማጣሪያን በመገንባት እየተሰራ ሲሆን፥ ይህም ዘላቂነት ያለውና ከአካባቢ ጋር የተስማማ ኢንዱስትሪን እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳሬክተሩ ገለጻ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ በውጪ ንግድ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና ዳሬክተር ካላብሮ አውሬሊያ በተወካያቸው ጽጋቡ ተካ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ትብብር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ በሆነ መንገድ ዘላቂና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ይፋ ለተደረገው ፕሮጀክት መሳካትም የልማት አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።