በአስር ከተሞች የተካሄደ የከተማ መሬት የሊዝ ገበያ ጥናት ይፋ ተደረገ

66

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጋር በመተባበር በ10 ከተሞች ያካሄደውን የከተማ መሬት የሊዝ ገበያ ጥናት ይፋ አደረገ።  

"የከተማ መሬት የሊዝ ገበያ ባህርያት በኢትዮጵያ" በሚል መነሻ በሀገሪቱ በሚገኙ የተመረጡ አስር ከተሞች ላይ የተካሄደው የከተማ መሬት የሊዝ ገበያ ባህርያት ጥናት ይፋ ተደረገ።

የጥናቱ ዋና ዓላማ በከተሞቹ የሚታየውን የሊዝ መሬት አሰጣጥ ችግሮች በመፍታት የተሻለ መሬት አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡

ግኝቱ ችግሮቹን በመፍታት በቀጣይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወት የሚያግዝ መሆኑ ተብራርቷል።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር እዩኤል ታምራት እንዳሉት በሊዝ ጨረታ መሬት ለመውሰድ አሸናፊ ከሆኑት 636 ተጫራቾች መካከል ጥናቱ በተደረገበት ወቅት 71 በመቶ የሚሆኑት ስራ አልጀመሩም። 

በ2014 ዓ.ም ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት መሬት ለመውሰድ ተጫርተው በሊዝ አሸናፊ የሆኑ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ደረጃ የያዙ 636 ተጫራጮች ተካተዋል፡፡

እንዲሁም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የተሰነደ የመስሪያ ቤቶች መረጃ በግብዓትነት መወሰዱን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ባህርዳር፣ ሐረር፣ ሀዋሳ፣ ጂግጅጋ እና ሰመራ ከተሞች በሊዝ ጨረታ መሬት በወሰዱ ግለሰቦችና በመሬት ተቋማት ላይ ጥናቱ መካሄዱን ተናግረዋል።    

የግንባታ ግብዓት እጥረት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ፣የመሰረተ ልማት አለመሟላት በዋናነት ወደ ስራ ላለመግባታቸው ምክንያት  መሆኑን መሬት የወሰዱ ግለሰቦችና ተቋማት መናገራቸውን አስረድተዋል።

የመረጃ አያያዝ ችግር ፣ ከተጫራቾቹ አንጻር የሚቀርበው መሬት አነስተኛ መሆን፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራው አነስተኛ መሆን በሊዝ ጨረታ መሬት በሚቀርብበት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች መሆናቸው በጥናቱ መለየቱን ተናግረዋል።

የሊዝ ጨረታ ካሸነፉ በኋላ መሬት ወስዶ ወደ ስራ ለመግባት ከአንድ ዓመት ጊዜ በላይ እንደሚፈጅ ጠቁመዋል።

የሊዝ ዋጋው በከተሞች መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለውና ለጨረታ በሚቀርብ የሊዝ መነሻ ዋጋ እና በሚያሸንፈው መካከል እስከ 50 እጥፍ ልዩነት መኖሩ በጥናቱ ተመላክቷል። 

በሊዝ ከሚተላለፉት ቦታዎች አብዛኛዎቹ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ያልተሟላላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ጥናቱ በከተሞቹ የመሬት አጠቃቀም ችግር መኖሩን ያመላከተ ሲሆን የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ለከተሞች ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ግኝቱን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

የተቀናጀ ዘመናዊ የሊዝ ስርዓት መዘርጋት ፣ የተጀመሩ የዲጂታል ስርዓቶችን የበለጠ ማጠናከር ፣በመሬት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አቅም ማጠናከር እንደ መፍትሄ መውሰድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

መሬት በሊዝ ጨረታ ከመተላለፉ በፊት በቂ መሰረተ ልማት ማሟላት እንደሚገባና የተላለፈው ቦታ በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን በተመለከተ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሊዝ መረጃን በአግባቡ መያዝ ፣የሊዝ ጨረታ ሲወጣ ማህበራዊ ሚዲያንና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ተደራሽ ማድረግ እና ግልጸኝነት ማስፈን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በሊዝ መሬት ወስደው ወደ ልማት ባልገቡ አካላት ላይ የሚመለከተው ተቋም በሚያከናውነው የክትትልና ቁጥጥር መላላት በ 95 በመቶ በሚጠጉት ላይ እርምጃ አለመወሰዱ በጥናቱ ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም