ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ክፍያ በሚጠይቁ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላልተገባ ወጪና እንግልት ተዳርገናል - ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች

67

  አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ክፍያ በሚጠይቁ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላልተገባ ወጪና እንግልት ተዳርገናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

የመዲናዋ የትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ ከታሪፍ ውጪ በሚያስከፍሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የከተማ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በአብዛኛው ከትራንስፖርት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው። 

በመዲናዋ ካለው የትራንስፖርት እጥረት ጋር በተያያዘ ሥራ አርፍዶ መግባት፣ አምሽቶ ወደ ቤት መመለስና ላልተገባ የታሪፍ ክፍያ መዳረግ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ፈተና ሆነዋል።

በርካታ የታክሲ አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው ከሕግ አግባብ ውጪ በራሳቸው ታሪፍ በማውጣት አስቀድመው፣ ይኼንን ያህል ትከፍላላችሁ በማለት ኅብረተሰቡን ላልተገባ ወጪ ሲዳርጉት ይስተዋላል።

ኢዜአ በተለይም በስራ መግቢያና መውጫ ወቅት ያለውን የትራንስፖርት ሁኔታ ለመቃኘት በመገናኛ ፤ አራት ኪሎ ፤ጊዮርጊስ፤አውቶብስ ተራና አዲሱ ገበያ ቅኝት አድርጓል። 

በዚሁ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡ ተገልጋዮች ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ክፍያ በሚጠይቁ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላልተገባ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።


 

አቶ አማረ መኮንንና አቶ ዩዲ መዲ የተባሉ ታክሲ ተጠቃሚዎች በተለይም በስራ መግቢያ፣ መውጫና በዓል ወቅት "ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ሕጋዊ እየመሰለ "መጥቷል ብለዋል።

ህብረተሰቡን በቀናነት የማገልገል ኃላፊነት እንዳለባቸው በመዘንጋት ህብረተሰቡን ማጉላላት ምርጫቸው ያደረጉ የታክሲ አሸከርካሪና ባለንብረቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የሚመለከተው የመንግስት አካል በትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ላይ እየደረሰ ለሚገኘው እንግልት ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

አቶ አብዲ ሙክታርና ተማሪ ኮከብ ደስታ በበኩላቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የሚጠይቁት ያልተገባ ክፍያ ተገልጋዩ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።

ተገልጋዮቹ የሚመለከተው አካል የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የብዙሃን ትራንስፖርትን ጨምሮ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት በማሳሰብ ተጨማሪ የትራንስፖርት አገልገሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎችን በመመደብ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።


 

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ እንዳሉት፤ በመዲናዋ ምስጉን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እንዳሉ ሁሉ የሥነ-ምግባር ጉድለት የተላበሱ አሽከርካሪዎች ጥቂት አይደሉም።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከታሪፍ በላይ ማስከፈልን ጨምሮ መስመር በማቆራረጥ ዜጎችን ለእንግልት ሲዳርጉ በተገኙ የታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ 67 ሺ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል።

በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ ጫና እያሳደረ የሚገኘውን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሻሻል የብዙኅን ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዜጎችን ላልተገባ ወጪና እንግልት በሚዳርጉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ክትትል በማድረግ ቀጣይነት ያለው አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በቀጣይም የትራንስፖርት አቅርቦትና ፍላጎቱን ለማጣጣም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራንስፖርት የስራ ስምሪት ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም