ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

181

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2016 (ኢዜአ)፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቴን ክሪስተንሰን ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በልማት ትብብር፣ በዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ለመቋቋም በሚከናወኑ ሥራዎች፣ በውኃ ሀብት አስተዳደር እና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች አጠቃቀም ዙሪያ የሁለቱን አገራት ትብብር ለማጠናከር ምክክር ተደርጓል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ኖርዌይ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ አጋር መሆኗን ገልጸው፤ ይህን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አንስተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በውኃ ሀብት አጠቃቀም እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ዙሪያ የሁለቱ አገራት ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

አምባሳደር ስቴን ክሪስተንሰን በበኩላቸው አገራቸው በተለይ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት በደን ልማት ድጋፍ በኩል አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

አምባሳደር ስቴን ክሪስተንሰን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በሁሉም ዘርፎች አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም