የመዲናዋ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

79

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ፡፡

የመዲናዋ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍቅሬ ግዛው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የዓለም 3ኛ የዲፕሎማቲክ ማዕከልና ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስባት ከተማ ናት፡፡

ኮሚሽኑ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ፣ የተቀናጀና የተደራጀ የአደጋ ቅድመ መከላከልና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት የመዘርጋት ተግባራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የእሳት፣ የጎርፍ፣ የመኪና፣ የህንጻ መደርመስና የመሬት መንሸራተት በመዲናዋ ተደጋግመው የሚከሰቱ አደጋዎች በመሆናቸው ይህንኑ የሚመጥን ስራ መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡

ኮሚሽኑ በ2022 ዓ.ም በአደጋ መከላከል፣ ቅነሳ እና መልሶ ማቋቋም በአፍሪካ ምርጥ የተሞክሮ ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ኮሚሽኑ ተልዕኮውን ለማሳካት አሁን ላይ በተቋሙ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች መጀመሩን ጠቁመው፤ ከዚህ ጎን ለጎን ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ ጥናትና ምርምር፣ ስልጠና፣ ማማከር፣ ትምህርት፣ የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር የትብብር ማዕቀፎችን መያዙን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ተቋማት በማህበረሰብ ደህንነት ጉዳይ ራዕይ ይጋራሉ ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በስኮላርሺፕ፣ በስልጠና በማማከር እና በመሰል ዘርፎች ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም