ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ውጤታማነት እንደግፋለን-  የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች

201

ቦንጋ ፤ሚያዚያ 10 /2016 (ኢዜአ)፡- ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ውጤታማነት ከድጋፍ ባሻገር የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ገለጹ።

የኮሚሽኑን ምንነትና ዓላማ ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቂ ግንዛቤ ኖሮት ተሳትፎ እንዲያደርግ የተጀመረው ስራ መጠናከር እንዳለበት ተመልክቷል።

ከአገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ በየነ በቀለ፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዘመናትን ለተሻገሩና ያለመግባባት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች መቋጫ መፍትሄ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ መረዳታቸውን ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ ስራ ግቡን እንዲመታ ግንዛቤ በመፍጠርና ተሳትፎ በማድረግ እንዲሁም አስፈላጊ በሆነ ሁሉ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።


 

ሀገራችን ለዘመናት ሲንከባለሉ በመጡ ችግሮች ሳቢያ ላለመግባባትና ለተለያዩ ችግሮች ተዳርጋለች ያሉት ደግሞ ሌላኛው የቦንጋ ከተማ የአገር ሽማግሌ አቶ አሰፋ ገብረማሪያም ናቸው። 

ለዚህ በምክክር ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ  ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ያለው  የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሚበረታታና ለተፈጻሚነቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ አበረክታለሁ ብለዋል።

አለመግባባቶችን መፍታት የምንችለው  በራሳችን አቅምና በጋራ ውይይት ነው ሲሉ ገለጸዋል።

ለዚህ እያመቻቸ ያለው ኮሚሽኑ ችግሮችን በሶስተኛ ወገን ሳይሆን በቀጥታ ከህብረተሰቡ ጋር በመገናኘት መፍትሔ ለማፈላለግ ወደ ተግባር መግባቱን እንደሚደግፉ  ገልጸዋል።  

ይህን ታሪካዊ እድል በተገቢው በመጠቀም በሰለጠነ አካሄድ በጋራ ተወያይቶ  ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት እንደሚያስፈልግም አቶ አሰፋ አመልክተዋል።

በዚህም ሰላሟ የተጠበቀ፣ አንድነቷ የጠነከረ እና ለሁሉም ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ላይ በጋራ መረባረብ ይገባናል ብለዋል።

ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት የሁሉም ህብረተሰብ የነቃ ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት የአገር ሽማግሌዎቹ፣ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ተሳትፎ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማ  ከግብ እንዲያደርስ እንደ የነገ ሀገር ተረካቢ  ወጣት ንቁ ተሳታፊ በመሆን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ያለው ደግሞ  ወጣት ዳንኤል መኩሪያ ነው።

ወጣቶች ከምንም  በላይ ስለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት ማሰብ ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው ያለው ወጣቱ፣ በተለይ ሀገራዊ አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን በምክንያታዊነት ከኮሚሽኑ ጎን መቆም ይገባናል ብሏል።


 

"እኛ ወጣቶች ከሚለያዩን ነጠላ ትርክቶች ነፃ በመሆን ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆን ይገባናል" ያለችው ደግሞ  ወጣት ፅጌ ግዛው ናት።

በሀገር ጉዳይ እንደማንኛውም ዜጋ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የኮሚሽኑ ስራ ፍሬያማ እንዲሆን ወጣቶች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም