ቀጥታ፡

በቡና ምርት አቅርቦት የአገሪቱን ዓለም አቀፍ ተሳትፎን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል- የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን

ዲላ ፤  ሚያዝያ 10 ቀን  2016 (ኢዜአ) ፡- በኢትዮጵያ   የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ዓለም አቀፍ ገበያ የምርት አቅርቦት  ተሳትፎን  ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።

የቡና ምርትና ምርታማነት ላይ ተሞክሮን ለመለዋወጥ  ከፌዴራልና ቡና አብቃይ ከሆኑ የአገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ የዘርፉ የስራ ሃላፊዎች፣ አርሶ አደሮችና የምርምር ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበት የመስክ ምልከታ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ እየተካሄደ ነው።


 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን  ምክትል  ዋና ዳይሪክተር አቶ ሻፊ ኡመር በወቅቱ እንዳሉት፤ በቡና እድሳት በተለይ ያረጀን ነቅሎ በተሻሻሉ ዝሪያዎች በመተካትና በመጎንደል የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝቷል።

ይህንንም ተሞክሮ አስፋፍቶ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የምርት አቅርቦት ተሳትፎዋን ከፍ ለማድረግ  ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የመስክ ምልክታውም በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በኩታ ገጠም የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎች ልማት የተገኘውን ውጤት ለማስፋት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ በሄክታር ከ19 ኩንታል በላይ ምርት መገኝቱን ገልጸው፤ ይህም ከአገራዊ አማካይ አንጻር ከፍተኛ በመሆኑ  ይህንን ልምድ ወስዶ ለማስፋፋት  ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የቡና ልማት ስራዎች በሄክታር 6 ኩንታል የነበረውን አማካይ ምርታማነት በተያዘው ዓመት ወደ 7 ነጥብ 4 ማሳደግ መቻሉን ያነሱት ደግሞ  የደቡብ ኢትዮጱያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ ናቸው።


 

ከዚህም በተያዘው ዓመት ከ32 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ባለፉት ወራት በተደረገ ጥረት ከ50 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

በክልሉ በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ የተገኘውን ምርታማነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም  በተያዘው  ወር ከ32 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎችን ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁንም ጠቅሰዋል።

የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ታጠቅ ዶሮ በበኩላቸው፤  በዞኑ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የኩታ ገጠም የቡና ልማት በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ የአረጀ ቡናን አንስቶ የተሻሻሉ ዝሪያዎችን እንዲተካ በማድረግ አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም