የቴክኖሎጂ እድገትን ተከትሎ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የብሪክስ አባል ሀገራት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል - ኢመደአ

177

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- የቴክኖሎጂ እድገትና ምጥቀትን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የብሪክስ አባል ሀገራት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(ኢመደአ) አስታወቀ።

ኢትዮጵያን በመወከል የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ እና ልዑካቸው በሩሲያ በተካሄደው 10ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ‘የወርኪንግ ግሩፕ’ መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት ዋና ዳይሬክተሯ የቴክኖሎጂ እድገትና ምጥቀትን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የብሪክስ አባል ሀገራት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

10ኛው የብሪክስ የወርኪንግ ግሩፕ ስብሰባ ‘Security in the use of Information and Communications Technologies’ በሚል መሪ ሀሳብ ሁሉም የብሪስክ አባል ሀገራት የዘርፉ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው የተካሄደው።

ኢትዮጵያ ከጃንዋሪ 1/2024 ወዲህ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ይታወቃል።

በዚሁ መድረክ ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነች ያለውን ተግባራት ያነሱት ወይዘሮ ትዕግስት ብዙ ወጣት የሰዉ ሀይል እንዳላት ሀገር ኢትዮጵያ የወጣቱን ተሰጥኦ እና የፈጠራ ስራ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ የራሱን ሚና እንዲወጣ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በፍጥነት ከሚለዋወጠው የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ስነ-ምህዳር ጋር ራሳችንን በፍጥነት ማላመድና እኩል መጓዝ ካልቻልን የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እድገትን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ከሚመጣው የሳይበር ጥቃት አደጋ ማንም ሊጠብቀን አይችልም ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት የብሪክስ አባል ሀገራትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የዓለም ሀገራት የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ዋና ጉዳያቸው ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም የኢንፎርሜሽን ደህንነት ጉዳይ በቀጣይም የብሪክስ አባል ሀገራትም ወሳኝ የውይይት አጀንዳ ሆኖ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ሀገራት በሳይበር ምህዳሩ ላይ ትብብርና ቅንጅቶችን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ምርጫችን ሊሆን ይገባል ሲሉም አክለዋል ወይዘሮ ትዕግስት በንግግራቸው።

የብሪክስ አባል ሀገራት የሳይበር ጥቃት ስጋቶችን የመቋቋም አቅማቸውን በማጠናከር የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ ዓለም አቀፋዊ ዲጂታል አካባቢን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በ10ኛው የብሪክስ የወርኪንግ ግሩፕ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ አባል ሀገራቱ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ደህንነት፣ የመረጃ ልውውጥ፣ የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል፣ የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች ለማከናወን፣ የሳይበር ጥቃትን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም የተሻሉ ልምዶችን ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ወይዘሮ ትዕግስት ከመድረኩ ጎን ለጎን ከተለያዩ የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ላይ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም