የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲይዙ የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል- የሰላም ሚኒስቴር

164

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡-የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲይዙ የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

የሰላም ሚኒስቴር "ዘመኑን የዋጀ አርበኝነት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ከዩንቨርሲቲ ምሁራን ጋር ውይይት እያካሔደ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ "አደዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ከ40 በላይ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት መካሔዱን አስታውሰዋል።

በመድረኩም የጋራ ማንነት፣ የጋራ እሴት እና አገራዊ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ስኬታማ ውይይቶች እንደነበሩ ገልጸው በቀጣይ ለሚካሔዱ የንቅናቄ መድረኮች ትልቅ ግብአት ተገኝቶበታል ብለዋል።

"ዘመኑን የዋጀ አርበኝነት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ይፋ የተደረገው ንቅናቄም በተመሳሳይ መልኩ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።

በሁሉም ዘርፍ ለሀገር ልማትና ብሄራዊ ጥቅም ታማኝ ሆኖ መስራት ከዜጎች ሁሉ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ገልጸው በተለይም ምሁራን በዚህ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች የጋራ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ በኩልም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የላቀ ሚና ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በመድረኩ "አደዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ሪፖርት ቀርቧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም