በአዲስ አበባ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ  ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ የሚካሄድ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ድዳ ድሪባ፤ በሰጡት መግለጫ ከተማ አቀፉ የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ  "ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በመሪ ሃሳብ ይካሄዳል ብለዋል።

የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄው ከነገ ሚያዚያ 11 ቀን 2016 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም የሚካሄድ  መሆኑንም ተናግረዋል።

የመረሃ ግብሩ ማስጀመሪያም በነገው እለት በአድዋ ድል መታሰቢያ  የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የህብረተሰብ ተወካዮችና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት በይፋ የሚጀመር መሆኑን ጠቁመዋል። 

ለስድስት ወራት በሚዘልቀው የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ መረሃ ግብር ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የተለያዩ ብክለቶችን የመከላከልና ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ መሰረት በሚያዚያ ወር በዋነኝነት የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል በየቦታው የተጣሉ ፕላስቲኮችን የማስወገድ ስራ ሲከናወን በግንቦት ደግሞ የአየር ብክለትን መከላከል ላይ ይተኮራል ነው ያሉት።

በመቀጠልም በሰኔ የውሀ ብክለትን ለመከላከል ወንዞችን የማጽዳት፣ በሃምሌ የአፈር ብክለትን፣  በነሃሴ የድምፅ ብክለትን የመከላከል ስራዎች የሚከናወኑ መሆኑ ተመላክቷል።

በመጨረሻም በመስከረም ወር በማህበራዊ ዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎች የሚያደርሱትን ተጽእኖ በመገምገም የንቅናቄ መርሃ ግብሩ የሚጠናቀቅ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም