በዞኑ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች ወደ ስራ እየገቡ ነው

61

ጉጂ ፤ሚያዝያ 10/2016 (ኢዜአ)፦ በጉጂ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች ወደ ስራ እየገቡ መሆኑ ተገለጸ።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በዞኑ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፈቃድ መሰጠቱን የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መብራቱ ሮቤ፣ ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች  103 መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ፈቃዱን የወሰዱት ባለሀብቶች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግንባታ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን ፍለጋና ግብይት የኢንቨስትመንት አማራጮች መሆኑን በማከል፡፡

የምርጥ ዘር ብዜትና ስርጭት፣ የቡና ኢንዱስትሪና ልማት፣ ሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም እንስሳት እርባታም በባለሀብቶቹ ትኩረት የተሰጣቸው ስራዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለሀብቶቹ መሰረተ ልማት የተሟላለት ከ276 ሄክታር በላይ የኢንቨስትመንት መሬት በመረጡት አካባቢ መውሰዳቸውንም አስታውሰዋል፡፡ 

የባለሀብቶቹ የልማት ስራዎች ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የማስገኘት አቅም እንዳላቸውም እንዲሁ፡፡

የአብዛኞቹ ባለሀብቶች በግንባታ ሂደት ላይ ሲሆኑ የተወሰኑት ማምረትና አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዞኑ የአዶላ ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ በራቆ፣ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበው በ75 ሄክታር መሬት በምርጥ ዘር ብዜትና ስርጭት የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ለዘንድሮ በልግ አዝመራ ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ድርጅት ተረክበው ያባዙትን 1 ሺህ 600 ኩንታል ምርጥ ዘር ለዞኑ አርሶ አደሮች አሰራጭተዋል፡፡

እስካሁን በዞኑ 5 ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የተሻሻሉና ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ ሶስት የበቆሎ ምርጥ ዘር ዓይነት ማሰራጨታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን ከሄክታር እስከ 300 ኩንታል ምርት የመስጠት አቅም ያለው የድንች ምርጥ ዘር እያባዙ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ 

ሌላው ባለሀብት አቶ ሙሉጌታ መሀመድ 40 ሚሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸው 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት የድንጋይ መፍጫ ማሽን ከቀረጥ ነጻ እንዳስገቡ ተናግረዋል፡፡ 

በተሰማሩበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከ30 ለሚበልጡ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ማስገኘታቸውን ተናግረዋል። 

በ19 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአዶላ ከተማ በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችላቸውን የግንባታ ስራ በማፋጠን ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ አሳምነው አለማየሁ ናቸው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም