በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ስድስት ዓመታት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርገዋል

63

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡-በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ስድስት ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ ስኬታማ ዐበይት የዲፕሎማሲ ትሩፋቶችን፣ በሳምንቱ የተከናወኑ እና ቀጣይ ሊከናወኑ የታሰቡ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ተግባራትን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም፥ ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ያስቻሉ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር መሰረት የሚጥሉ ስራዎችን በስፋት መስራቷን አንስተዋል።

ለአብነትም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬታማ የግንባታ ሂደት ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ዳያስፖራው በነዚሁ የለውጥ ዓመታት ለተለያዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና የልማት መርሀ ግብሮች እስከ 100 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ20 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ቤት መላካቸውንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም