የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪን ዘላቂ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

66

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2016 (ኢዜአ)፦የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፤ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ በሆነ መንገድ ዘላቂ ተወዳዳሪ የሚሆኑነትን ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ አውደ ጥናት ላይ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ፕሮጀክቱ በመንግስትና በልማት አጋሮች የተቀረጸ ሲሆን የአካባቢ ደህንነትን ማስጠበቅ ዋነኛ አላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳሬክተር ስለሽ ለማ፤ የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን መልሶ ለመጠቀም፣ ለዘላቂ የኬሚካል አያያዝ፣ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ፕሮጀክቱ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ለማስወገድና ከአካባቢ ጋር የሚስማማ የምርት ሂደት እንዲኖርም ያደርጋል ብለዋል።

ለባለሃብቶች የምርትና አገልግሎት ተወዳዳሪነት፣ ወጪ ቆጣቢነትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

ለቀጣይ አምስት አመታት በጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራች ዘርፍ ላይ ተግባራዊ የሚሆነው ይህ ፕሮጀክት በቀጣይ ወደ ሌሎች ዘርፎችም የሚሰፋ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም