በአፋር ክልል ከስድስት ሺህ በላይ ተገልጋዮች ብሔራዊ መታወቂያ ወስደዋል - የክልሉ ገቢዎች ቢሮ

67

ሠመራ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል ስድስት ሺህ 127 ተገልጋዮች ብሔራዊ መታወቂያ  መውሰድ መቻላቸውን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ አቶ አወል አብዱ አወል አስታወቁ።

እንደ ሀገር በተያዘው አቅጣጫ መሠረት ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ  ከሐምሌ 18 ቀን 2015ዓ.ም ጀምሮ ስራው በክልሉ እየተከናወነ መሆኑ ታውቋል።

በዚሁ መሠረት ለዜጎቹ ብሔራዊ መታወቂያው እንዲሰጥ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ አወል አብዱ አወል ገልጸዋል።

በክልሉ በሶስት ማዕከላት ማለትም በክልል ገቢዎች ቢሮ፣ በሠመራ ከተማ አስተዳደር እና በአዋሽ ከተማ አስተዳደር አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም በክልሉ ስድስት ሺህ 127 ተገልጋዮች ብሔራዊ መታወቂያ  መውሰድ ችለዋል ብለዋል።

ማህበረሰባችን አገር አቀፍ ደረጃ ያለውን መታወቂያ መያዙ እንደ ዜጋ  ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ይህም አገሪቷ ለተያያዘችው የተሻለ አገልግሎት መሥጠት የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

አገልግሎቱን በቀጣይነት በማስፋት ዞንን ማዕከል በማድረግ ለሁሉም ወረዳዎች ተደራሽ ለማድረግ የታቀደ መሆኑንም ሃላፊው አስረድተዋል።

በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የብሄራዊ መታወቂያ ምዝገባ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው  ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር ተወግዶ መታወቂያው በፍጥነት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

እያንዳንዱ ግለሰብ በተመዘገበ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስልክ ቁጥሩ በአጭር መልዕክት እንዲደርሰው ተደርጎ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ እየተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

የብሄራዊ መታወቂያ የመሥጠቱ መርሃ ግብር እስከ ታች ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም