በክልሉ 500 ሚሊዮን ብር የተገነባ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ የማምረት ሥራውን ጀመረ

246

አሶሳ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን በ500 ሚሊዮን ብር የተገነባው የዮ ሆልዲንግ ዘመናዊ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ኩባንያ ምርት ማምረት ጀምሯል።

ኩባንያው አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ  ለክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላትና እና ለባለድርሻ አካላት ዛሬ በአሶሳ የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር አካሂዷል።


 

የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ታደሰ በወቅቱ እንዳሉት በ500 ሚሊየን ብር በካማሽ ዞን ምዥጋ ወረዳ የተገነባው  የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ወደ ሥራ ገብቷል።

የድንጋይ ከሰል ማምረቻው በዓመት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ ጥሬ ድንጋይ ከሰል የማቀነባበር አቅም እንዳለው አስረድተዋል::

እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴም 77 ሺህ 500 ቶን የከሰል ድንጋይ ምርት በማቀነባበር ለሀገር ውስጥ የሲሚንቶ፣ ብረታ ብረት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ወረቀት፣ ሴራሚክ እና ሌሎች ፋብሪካዎች ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

 ከ200 ለሚበልጡ ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው በቅርቡ ሁለተኛው ምዕራፍ  ሲጀመር የሠራተኞችን ቁጥር ወደ 700 እንደሚያደርስ አስታውቀዋል።

ማቀነባበሪያው በአካባቢው ስራ መጀመሩ በአካባቢው ማህበረሰብ የስራ ባህል በማሻሻል የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለውም ዋና ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል::

የቤንሻንገል ጉሙዝ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቃሲም ኢብራሂም በበኩላቸው የኩባንያው እንቅስቃሴ ለሌሎች ባለሃብቶች እና ኩባንያዎች ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ገልጸዋል።

የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ የተፈጥሮ ማዕድናትን በዘላቂነት ማልማት የሚቻለው ለአካባቢው ልዩ ትኩረት ስንሰጥ ነው ያሉት ሃላፊው፤ ኩባንያው በከሰል ማምረት ሂደት የአካባቢ ጥበቃ ህጎችን በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል::

ኩባንያው የምርት ሂደቱን እንዲያቀላጥፉ የተነሱ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ሃሳቦች ምላሽ እንደሚሰጥባቸው አረጋግጠዋል::

በመድረኩ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል::

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም