በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተካሄደ የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች 630 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ቃል ተገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተካሄደ የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች 630 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ቃል ተገብቷል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተካሄደ የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚውል የ630 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ቃል መገባቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በ3ኛው ምዕራፍ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳኡዲ ዓረብያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ4 ሺ200 በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉም ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ ስኬታማ ዐበይት የዲፕሎማሲ ትሩፋቶችን፣ በሳምንቱ የተከናወኑ እና ቀጣይ ሊከናወኑ የታሰቡ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ተግባራትን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፥ በሲዊዘርላንድ ጄኔቫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በተገኙበት የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መካሄዱን ገልጸዋል።
በዚህም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚውል 630 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ቃል መገባቱን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በ3ኛው ምዕራፍ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳኡዲ ዓረብያ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሰነድ አልባ ዜጎችን የመመለስ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዚህም ከሳኡዲ ዓረብያ ከ4 ሺ200 በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ይህ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮ-ሳኡዲ ዓረቢያ የሁለትዮሽ የሚኒስትሮች ጉባኤ በመጪው ግንቦት ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያና ጃፓን ያላቸውን የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በቶኪዮ ጃፖን ምክክር ማድረጋቸውንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አንስተዋል።
በብሪክስ ማዕቀፍ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የቴክኒክ ኮሚቴ ሦስተኛ ስብሰባ መካሄዱንም እንዲሁ።