ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በርካታ የቅድመ ዝግጅት እና የተሳታፊ ልየታ ስራዎችን አከናውኗል -ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

487

 አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 10/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በርካታ የቅድመ ዝግጅት እና የተሳታፊ ልየታ ስራዎች ማከናወኑን  ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

ለኮሚሽኑ የሚደረጉ ድጋፎች በሃገር ግንባታ ስራዎች ላይ አሻራ የምንጥልበት በመሆኑ አስፈላጊውን የቅንጅት ስራ መስራት አንደሚገባም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል፡፡

የሃገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የአራት ወራት የሥራ የአፈፃፀም ሪፖርት የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተገምግሟል፡፡  



በመድርኩ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አፈ -ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት የምክክር ኮሚሽኑ ሃላፊነትን በተላበሰ መልኩ ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ እና ለማረጋገጥ የሰራቸውን ስራዎች በጥንካሬ አንስተዋል።

በሀገር ደረጃ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ከችግሩ መቅድም ያስፈልጋል ያሉት አፈ -ጉባኤው ለሃገራዊ ምክክሩ ከመንግስት መዋቅርና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመመካከር እንዲሁም ሌሎች ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ተቋማት ጋር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በጋራ በመስራት ለሃገሪቱ ህዝብ የገባነውን ቃል መፈጸም ይኖርብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው በክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በርካታ የቅድመ ዝግጅት እና የተሳታፊ ልየታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በክልል ደረጃ የሚደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ቀሪ የምክክር ሂደቶችን አስመልክቶ የአሰራር ስርአት በመዘረጋት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ዋና ዋና ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።


 

በቀጣይም ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታ ባልተከናወነባቸው ክልሎች ልየታ በማድረግ አጀንዳዎችን በህዝባዊ ውይይቶች በማሰባሰብ ምክክሮች እንደሚካሄዱ ጠቁመው፤ በዚህ ሂደት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያግዙ የሀገር ሽማግሌዎችንና በማህበሩሰቡ መካከል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን የመለየትና ተቀራርቦ የመወያየት ስራዎችን እንሰራለን ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በምክክር ሂደቱ ውጤታማ እና በሃገሪቱ የተሻለ የሰላምና የፖለቲካ መደላድል እንዲፈጠር ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅዖ ሊያበረከት ይገባል ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በመድረኩ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ምክትል አፈጉባኤን ጨምሮ የመንግስት ተጠሪዎች፣ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና አባላት እንዲሁም የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ፣ ሚኒስትሮች እና ኮሚሽነሮች፣ የመገናኛ ብዙሃን ሀላፊዎችና  ሌሎችም የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች የኮሚሽኑን የአራት ወራት የአፈፃፀም ሪፖርት አዳምጠዉ ሃሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም