ቀጥታ፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ20 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ቤት ልከዋል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ20 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ቤት መላካቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከናወኑ ስኬታማ ዐበይት የዲፕሎማሲ ትሩፋቶችን፣ በሳምንቱ የተከናወኑና በቀጣይ ሊከናወኑ የታሰቡ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ተግባራትን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዜጋ ተኮር፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና መሰል ተግባራት የተገኙ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ክንውኖችን አብራርተዋል።

በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ በጋራ የመጠቀም ስኬታማ የዲፕሎማሲ ተግባር ማከናወናቸውን ተከትሎ የኖቤል ሽልማት ማግኘታቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ሰራዊት በደቡብ ሱዳንና ሱማሊያ እያከናወነ የሚገኘው ተልዕኮ ወሳኝ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት አመታት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በኩል በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ትብብር አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሔ በሚል እሳቤ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ፓን አፍሪካኒዝምን ጨምሮ ስኬታማ የልማት ትብብር መፈጠሩን አንስተዋል።

በምግብ ራስን ለመቻል በበጋ ስንዴ ልማት የተገኘው የግብርና ልማት ስኬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለተሰጣቸው ዕውቅና ማሳያ ነው ብለዋል።

ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ክፍት እየተደረገ የሚገኘው ገበያ የቴሌኮም ኢንዱስትሪውን ሊበራላይዝ በማድረግና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከጫና በማላቀቅ በስኬታማ ሂደት ላይ እንዲገኝ ማስቻሉን ገልጸዋል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እየሄደበት የሚገኘው ስኬታማ የግንባታ ሂደት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማሳለጥ መሰረት የሚጥል መሆኑን አንስተዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ስኬታማ ውይይትና ግንኙነት መፍጠር የተቻለበት ዓመት እንደነበርም አስታውሰዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በአማካይ በየዓመቱ 4 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በማሰባሰብ በስድስት ዓመት ውስጥ ከ20 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ቤት መላካቸውን ገልጸዋል።

በአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ በመከላከል ኢትዮጵያ የራሷን አሻራ እያሳረፈች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮ-ሳዑዲ ዓረቢያ የጋራ የሁለትዮሽ የሚኒስትሮች ጉባኤ በመጪው ግንቦት ወር እንደሚካሄድ የቀጣይ ዲፕሎማሲ ተግባራትን ባብራሩበት ወቅት አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም