ለዜጎች ብቻ ተከልለው የቆዩ የንግድ ስራዎች ለውጭ ባለሃብቶች መፈቀዳቸው ለሀገር እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነት ፋይዳው የላቀ ነው

175

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ተከልለው የነበሩት የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለሃብቶች መፈቀዱ ለሀገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንሸስትመንት ቦርድ በተከለሉ የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ስራዎች የውጭ ባለሃብቶች ኢንሸስትመንት ተሳትፎ አፈጻጸም መመሪያ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርአያስላሴ፤ በመግለጫቸው ለኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ተከልሎ የነበረው የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለሃብቶች መፈቀዱ በሚኖረው ፋይዳ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የግል ዘርፉን ሚና ለማሳደግ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው የአሁኑን መመሪያም ጠቀሜታና አስፈላጊነት አብራርተዋል።

ለዜጎች ብቻ ተከልሎ የነበረው የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለሃብቶች መፈቀዱ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ከአለም አቀፉ የንግድ ትስስር ስርዓት ጋር በስፋት እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲቀስሙ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ከለላ በተሰጣቸው ዘርፎች የአገልግሎት ተደራሽነት፣ የጥራት እና የብቃት ችግር መኖሩን ጠቅሰው ይህንንም ችግር የሚፈታ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ባካሄዱት ዝርዝር ጥናት በጉዳዩ ላይ መሰረታዊ የፖሊሲ ለውጥ እንዲኖር አድርጓል ብለዋል። 

በዚህም መሰረት በአራቱም የንግድ ስራ ዘርፎች ላይ የውጭ ባለሃብቶች መሳተፍ የሚችሉበት አዲስ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1001/2016 መፅደቁን ገልጸዋል። 

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ተከልሎ የነበረው የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ለውጭ ባለሃብቶች መፈቀዱ ለሀገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

የውጭ ባለሃብቶች ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟሉ ድረስ በጥሬ ቡና፣ በቅባት እህሎች፣ በጫት፣ በጥራጥሬ፣ በቆዳና ሌጦ፣ የደን ውጤቶች፣ የዶሮ እና የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ገበያ መሳተፍ የሚችሉ ይሆናል። 

ከማዳበሪያና ነዳጅ በስተቀር በሁሉም የገቢ ንግድ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይም መሳተፍ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ባለሃብቶችን ማመልከቻ በመቀበልና በመመሪያው በተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በመገምገም የንግድ ምዝገባ ያከናውናል፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድም ይሰጣል። 

በመመሪያው መሰረት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለተሰጣቸው የውጭ ባለሃብቶች የንግድ ስራ ፍቃድ ይሰጣል፣ የንግድ ስራ ሂደቶችንም የሚቆጣጠር ይሆናል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም