በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመማሪያ መጽሐፍት እጥረትን ለማቃለል ርብርብ እየተደረገ ነው

181

ጂንካ/ሶዶ ፤ ሚያዚያ 10/ 2016(ኢዜአ) ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለአንድ ተማሪ አንድ መጽሕፍ በማዳረስ የመጽሐፍት እጥረቱን ለማቃለል  ማህበረሰብን በማሳተፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

 በክልሉ ''አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ''በሚል መሪ ሀሳብ በተጀመረው የሀብት ማሰባሰብ ንቅናቄ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ መሰብሰቡን ቢሮው አስታውቋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ስምዖን ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የመማሪያ መጻህፍት እጥረትን ለማቃለል  የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። 

ከዚህ ውስጥ  በርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረውና ለአንድ ወር ቆይታ የሚኖረው የ"አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ" የሀብት  ማሰባሰብ ንቅናቄን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን በቅድመ መደበኛና በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ተማሪ አንድ መጽሕፍ በማዳረስ የመጽሐፍት እጥረቱን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑ አስረድተዋል።

ለመጽሕፍት ሕትመቱ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 30 በመቶ  መንግስት፤ ቀሪ 70 በመቶውን ደግሞ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ሀብት ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ በሚገኙ 12 ዞኖች በአንድ ሳምንት በተደረገው ንቅናቄ እስካሁን ወደ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ መሰብሰቡን አመልክተው፤ ከማህበረሰቡ፣ ከተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ሀብት የማሰባሰቡ ጥረት ይቀጥላል ብለዋል ።

ቀደም ብሎ በተካሄደው የንቅናቄው ማስጀመሪያ መረሃ ግብር  የክልሉ መንግስት የ300 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ከቀጣይ ወር ጀምሮ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ክፍሎች የመማሪያ መጽሕፍት ህትመት ይጀመራል ሲሉ ገልጸዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመጽሕፍት እጥረት ችግር ለመፍታትም  ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘንድሮ  ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ  የመማሪያ መጽሕፍት በሚኒስቴሩ በኩል ታትመው በክልሉ ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቶች መሰራጨታቸውንም  አቶ ስንታየሁ አመልክተዋል።

የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ኩማ በበኩላቸው ፤"አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ" በሚል መሪ ሃሳብ የተጀመረው ሀብት የማሰባሰብ ንቅናቄ በዞኑ ባሉ ትምህርት ቤቶች ያጋጠመውን የመፅሐፍ እጥረት ለማቃለል የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአንድ ወር በሚቆየው ሀብት የማሰብሰብ ንቅናቄ ከ314 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ከዞኑ ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክተው፤ እስካሁን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በንቅናቄው በማሳተፍ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

 ''አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ''በሚል ማህበረሰቡን ያሳተፈ ንቅናቄ በሁሉም የዞኑ አከባቢዎች መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የአሪ ዞን የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳግም መኮንን ናቸው። 

በዞኑ 250 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቶ  ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  ቅድመ መደበኛን ጨምሮ ከ1ኛ እስከ 12ኛ የክፍል ደረጃዎች ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታው ላይ እንደሚገኙ ከትምህርት ቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም