ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ያልተቆጠበ ትብብር እናደርጋለን--የምስራቅ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች

232

ሀዋሳ ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ያልተቆጠበ ትብብር እናደርጋለን ሲሉ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሻሸመኔ ክላስተር ከምስራቅ ጉጂ ዞን በወረዳ ደረጃ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክር ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን መረጣ እያካሄደ ነው።


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል በሀሮ ወለቡ ወረዳ ቡርቂቱ መርመራ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ደስታ ቡልጡ እንደገለጹት፣ በሀገራችን ለዓመታት ባልተፈቱ ቅራኔዎችና የጥላቻ ትርክት የሰላም እጦት በተደጋጋሚ ሲከሰት ይስተዋላል።

በዚህም የሰው ህይወት እየተቀጠፈ፣ ንብረት እየወደመ እና ዜጎችም ከቄያቸው በመፈናቀል እንደሀገር ዋጋ እየተከፈለ መሆኑን እስታውሰዋል።

ለዘመናት ያልተፈቱና ላለመግባባት እንቅፋት የሆኑ ችግሮች በቀጣይም ለህዝቦች አንድነት ፈተና ሆነው እንዳይቀጥሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም ለኮሚሽኑ ሥራ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለጹት አቶ ደስታ፣ በተለይ የወረዳ የህብረተሰብ ተወካይነትን ዕድል ካገኙ የህብረተሰቡ የጋራ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።    


 

ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ወርቅነሽ ገልቹ በበኩላቸው፣ ለልዩነት ምክንያት የሆኑ ውስብስብ ችግሮችን ፈትቶ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

"ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋል" ያሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ፣ አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማሳተፉ የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል ብለዋል።

በተለይ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት አገራዊ አንድነትን ለማምጣት ሚናው የጎላ በመሆኑ ከኮሚሽኑ ጎን ሆነው ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።      

በዞኑ የዋደራ ወረዳ የሃይማኖት አባቶችን ወክለው በመድረኩ ላይ የተሳተፉት መላከሰላም ቀሲስ አለነ ቀለመወርቅ በበኩላቸው ዘመናትን የተሻገሩ ቁርሾዎች የወለዱት አለመግባባቶች በምክክርና በውይይት እንዲፈቱ መንግስት ትኩረት መስጠቱን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

"ሁሉም ዜጋ ችግሮችን በንግግር እና በምክክር ይፈታሉ የሚል እምነት ሊኖረው ይገባል" ያሉት መላከ ሰላም ቀሲስ አለነ፣ ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኦሮሚያ ተሳታፊ ልየታ ቡድን አስተባባሪ አቶ ብዙነህ አስፋ  ሀገራዊ ምክክሩ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትና አገራዊ አንድነት ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በየደረጃው የሚካሄደው ምክክር ወጤት እንዲያመጣ ህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት የገለጹት አስተባባሪው የምክክሩ ውጤታማነት በውይይቱ ተሳታፊዎች አስተዋጾ እንደሚወሰን አስገንዝበዋል።

ለልዩነትና ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመሰረታዊነት ፈትቶ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። 

በኦሮሚያ ክልል የተሳታፊ ልየታ ሥራ በአራት ክላስተሮች ተከፋፍሎ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ብዙነህ፣ እስካሁን በ282 ወረዳዎች ከ5 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ተወካዮች መለየታቸውን አስታውሰዋል።

ኮሚሽኑ በምስራቅ ጉጂ ዞን የህብረተሰብ ተወካዮችን ለመለየት ባዘጋጀው መድረክ ከ11 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ1ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም