በድሬዳዋ አስተዳደር ከመደመር ትውልድ ሽያጭ በተገኘ ገንዘብ የህዝብ ቤተመጻሕፍት እየተገነባ ነው

89

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገንዘብ የህዝብ ቤተ መጻሕፍት እየተገነባ መሆኑን የአስተዳደሩ  ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ገለጸ።

በ470 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የመደመር ትውልድ ቤተ መጻሕፍት በ18 ወራት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር)  ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ የተገኘው ገንዘብ በከተማዋ ለሚስተዋል ችግር መፍቻ ግንባታ እንዲውል ባበረከቱት ስጦታ መሠረት ነው ቤተ መጻሕፍቱ መገንባት የጀመረው ።

የድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መገንባት የጀመረው ባለ  ስድስት ወለል ቤተመጻሕፍት በተለይም የከተማው ወጣት በዕውቀት እንዲታነጽ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ቤተ መጻሕፍቱ  ዋናውን ቤተ መፅሐፍ ጨምሮ የተለያዩ የማንበቢያ ክፍሎች በውስጡ አካቷል ብለዋል።

በተጨማሪም ለካፍቴሪያ አገልግሎት እንዲሁም የአስተዳደሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በጥናትና በምርምር ወደ ተሻለ ከፍታ ለማስጓዝ የሚያግዙ ክፍሎች በውስጡ ማካተቱን ነው የገለፁት።

የመጽሐፍ መሸጫዎች፣ የአይቲ ክፍሎች፣ የውጭ ማንበቢያ ቦታዎችና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ከፍሎች እንደሚኖሩት አስረድተዋል ።

በ470 ሚሊዮን ብር መገንባት የጀመረው ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት በ18 ወራት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በዕውቀትና በክህሎት  የተገነባ አገር ገንቢ ትውልድ ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ  አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በዕውቀት የታነፀና በክህሎት የዳበረ ትውልድ ማፍራት የነገዋን የተሻለች አገር ለመገንባት  ወሳኝ በመሆኑ ሌሎችም ባለሃብቶችና በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች በመሠል ፕሮጀክቶች ላይ የድርሻቸውን በማበርከት የድሬዳዋን ከፍታ ዕውን እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።

የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ አቶ ሁሴን ጌታሁን  በበኩላቸው ግንባታው  ላይ  55  ወጣቶች ጊዜያዊ የስራ ዕድል አግኝተው ለቀጣይ ህይወታቸው መሠረት የሚጥል ዕውቀትና ክህሎት እየቀሰሙ ይገኛሉ ብለዋል።


 

አስተዳደሩ ለፕሮጀክቱ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ለፕሮጀክቱ መፋጠንና ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ነው  አቶ ሁሴን የገለፁት።

ከመደመር ትውልድ የመፅሃፍ ሽያጭ በተበረከተው ገንዘብ እየተገነባ የሚገኘው የመደመር ትውልድ ዘመናዊ ቤተ- መጻሕፍት ባለፈው መስከረም ወር  በአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም