በምዕራብ ሸዋ ዞን በመኸር አዝመራ ከ826 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ይለማል

80

አምቦ ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሸዋ ዞን በመኸር አዝመራ ከ826 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት ዝግጅት መጀመሩን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ጸጋዬ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2016/17 የመኽር ምርት ዘመን 826 ሺህ 236 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል።

በምርት ዘመኑ 29 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክተዋል።

ለግብርና ስራው ስኬታማነትም በዞኑ በሚገኙ 23ቱም ወረዳዎች የግብርና ባለሙያዎችን በማሰማራት ሙያዊ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር የማቅረብ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።  

በእስካሁኑ ሂደት 415 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለወረዳዎች መሰራጨቱን የገለጹት ደግሞ የዞኑ  የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ባለሙያ አቶ ዳኛቸው አለማየሁ ናቸው።

እንዲሁም 5 ሺህ ኩንታል ምርጥ የበቆሎ ዘር አቅርቦት ለወረዳዎች መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

በምእራብ ሸዋ ዞን በ2015/16 በመኸር ከለማው 824 ሺህ ሄክታር 28 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም