የልዩ ኢኮኖሚ ዞን እና የበይነ መንግስታዊ የልማት ባለስልጣን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች ፀደቁ

69

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፦የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን እና የበይነ መንግስታዊ የልማት ባለስልጣን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባው በሁለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጎ አጽድቋል።

በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪና ማዕድን እንዲሁም የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል።

በቀላሉ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የስራ ዕድል ለመፍጠርና አምራች ኢንዱስትሪውን ለማበረታታት ረቂቅ አዋጁ ጉልዕ ሚና የሚኖረው መሆኑ በረፖርቱ ተመላክቷል።

የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑም ተብራርቷል።



ቋሚ ኮሚቴዎቹ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮችን ማሻሻላቸውን ገልፀው ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም በረቂቅ አዋጁ ላይ ያላቸውን ሃሳብና አስተያየት በመስጠት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅን አጽድቀዋል።

የበይነ መንግስታዊ የልማት ባለስልጣን (ኢጋድ) ማቋቋሚያ ስምምነትን ለማሻሻል በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቷል።

የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረ በመሆኑ አብራርቷል።

በመሆኑም አሁን ካለው ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አኳያ መሻሻል አስፈላጊ ስለመሆኑ ያነሱ ሲሆን ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ መክሮ የተሻሻለውን ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም