በድሬዳዋ አስተዳደር ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሶስት ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ናቸው

53

ድሬዳዋ፤ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉት ችግኞች የአካባቢውን ውበትና ስነምህዳር ከመጠበቅ በዘለለ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ተግባራት እያገዙ መሆናቸውን የአስተዳደሩ የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ገለፀ።

የአካባቢ ጥበቃውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ለዘንድሮ ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሶስት ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው  ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል።


 

በድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ባለፉት ዓመታት በመርሃ ግብሩ  የተተከሉ ችግኞች የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ ለብሰው የተፈጥሮ ሚዛንና ስነምህዳር እንዲጠበቅ አግዘዋል።

አረንጓዴ በለበሱ አካባቢዎች ደግሞ የጠፉ ምንጮች እና የዱር አራዊቶች ተመልሰዋል ብለዋል።

በተለይም በገጠር ቀበሌዎች ለተደጋጋሚ ድርቅ የሚጋለጡ ማህበረሰብ ካበቀሏቸው የፍራፍሬ ዛፎች ተጨማሪ ገቢ በማግኘት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ ማገዛቸውን ነው የገለፁት።

ከድሬዳዋ ግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመቀናጀት እነዚህን ውጤቶች ወደ ተሻለ ውጤት ለማድረስ  በዘንድሮ ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሶስት ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን በ20 የገጠርና የከተማ ችግኝ ጣቢያዎች እየተባዙ ከሚገኙት ውስጥ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ችግኞች ደርሰው ለተከላ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በባለስልጣኑ የደን ልማት ቡድን መሪ አቶ ማሙሽ ዘውዴ በበኩላቸው ለዘንድሮ ክረምት እየተዘጋጁ ከሚገኙት አገር በቀል ችግኞች ውስጥ 50 በመቶዎቹ ለገጠሩ አየር ንብረት ተስማሚ  የሆኑ የፍራፍሬ ችግኞች በመሆናቸው የገጠሩን ህብረተሰብ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ይሆናሉ ብለዋል።

ድሬዳዋ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሶማሌ ክልል ሲቲ ዞንና ለምስራቅ ሐረርጌ የኦሮሚያ ወረዳዎች አስፈላጊውን የችግኝ ድጋፍ በማድረግ የተቀናጀ ውጤት እንዲመዘገብ እያደረገ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የአረንጓዴ አሻራና የተፋሰስ ልማት ስራዎችን በማቀናጀት በገጠር የተካሄዱ ልማቶች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ስራ ውጤታማ እያደረገው መሆኑን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ ናቸው።

አቶ ኑረዲን  እንዳሉት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሚተከሉ ችግኞች ግማሾቹ የአርሶ አደሩን የገቢ ምንጭ እያጎለበቱ የሚገኙ የተለያዩ ፍራፍሬዎች ናቸው።

ለድርቅ አደጋ የተጋለጡት  የገጠር ቀበሌዎች ያሉ አርሶ አደሮች ውሃን በቀላሉ በማግኘት ካመረቷቸው የፍራፍሬ ምርቶች ተጨማሪ ገቢ በማግኘት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ የጎርፍ  ምንጭና መነሻ ከሆኑት የምስራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች ጋር በመቀናጀት የተሰሩ ስራዎች ጎርፍን በመከላከልና ውሃውን ለልማት ለማዋል እያገዙ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ዘንድሮም እነዚህን የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች ለማሳደግ የዝግጅት ምዕራፍ እየተጠናቀቀ ይገኛል ብለዋል።

በአስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከስምንት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የዛፍ፣ የጥላ፣ የውበት እና የፍራፍሬ ችግኞች በገጠርና በከተማ የተተከሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 68 በመቶዎች ፀድቀው እቅዱን ማሳካት መቻላቸውን  መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም