የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ ይጀመራል

314

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

በ22ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ወልቂጤ በ16 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

በገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን በ19 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ምሽት 1 ሰዓት በሚደረገው የ22ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ሁለተኛ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና ይጫወታሉ።

ባህር ዳር ከተማ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፈም። በሶስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በ33 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል ።

ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው በአንዱ ተሸንፎ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ሀዲያ ሆሳዕና በ30 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የ22ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ነገ ቀጥሎ ሲውል ሀምበሪቾ ዱራሜ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት፤ ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።

ፕሪሚየር ሊጉን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ43 ነጥብ እየመራ ይገኛል።

የሃዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌይማን 12 ጎሎች በማስቆጠር የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ነው።

ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ቻርልስ ሙሲጌ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማኑኤል ኦርቦ፣ የባህር ዳር ከተማው ቸርነት ጉግሳ እና የአዳማ ከተማው ዮሴፍ ታረቀኝ በተመሳሳይ በ9ኝ ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ23ኛ እስከ 27ኛ ሳምንት ያሉ ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩንቨርስቲ ስታዲየም እንደሚካሄዱ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም