ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአካባቢ ብክለት ተጽእኖ ባደረሱ 1 ሺ 720 ተቋማት ላይ  እርምጃ ተወስዷል-ባለስልጣኑ

155

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 10/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአካባቢ ብክለት ተጽእኖ ባደረሱ 1 ሺ 720 ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ድዳ ድሪባ ለኢዜአ እንዳሉት ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ የቁጥጥር ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በዚህም በዘጠኝ ወራት 7 ሺ 294 ተቋማትን ለመቆጣጠር አቅዶ 7 ሺ 598 ተቋማትን በመቆጣጠር ከዕቅዱ በላይ ማሳካቱን ተናግረዋል፡፡

በተደረገው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በአካባቢ ላይ ብክለት ባደረሱ 1 ሺ 720 ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን አረጋግጠዋል፡፡

ከተቋማቱ መካከል 1 ሺ 661ዱ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት ተግባራቸውን ሳያከናዉኑ የቀሩ 59 ተቋማት መታሸጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለስልጣኑ የአካባቢ ተጽእኖን ለመቆጣጠር በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት ተቋማት ህጎችን  አክብረው እንዲሰሩ  የጀመረውን ቁጥጥርና ክትትል አጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም