የኢትዮጵያ ባህር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታዩበትን ክፍተቶች እንዲያርም ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

229

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ባህር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርትና የወደብ አገለግሎቶች አሰጣጥ ላይ የታዩበትን ክፍተቶች እንዲያርም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የድርጅቱን የ2014/15 ዓ.ም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተደረገ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በመድረኩም ድርጅቱ በወደቦችና ተርሚናሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያከናውናቸው ግዥዎች፤ የግዥ ሥርዓትና መመሪያን ያልተከተሉ መሆናቸው በክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል።

ድርጅቱ በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ከውጪ ሀገር በጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ውስጥ መዳረሻ ቦታዎች ለአጓጓዛቸው ጭነቶችና የተሽከርካሪ አገልግሎቶች ከደንበኞቹና ከተቋማት ያልሰበሰባቸው ውዝፍ ክፍያዎች መኖራቸው በክፍተት ተነስቷል።


 

በዚህም ድርጅቱ ከግለሰቦችና ከተቋማት ያልሰበሰበው ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ መኖሩን የተመላከተ ሲሆን ድርጅቱ ባለቤታቸው ያልታወቀና ጊዜ ያለፈባቸው ኮንቴነሮችን በጊዜ ከማስወገድ አኳያ ክፍተት እንዳለበትም ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል ደርጅቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊያሰራ የሚያስችል ድርጅታዊ መዋቅርና አስፈላጊው የሰው ኃይል ማሟላት ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት በኦዲቱ ተመላክቷል።

በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት በጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ውስጥ የሚጓጓዙ የኮንቴይነር ጭነቶችና ተሽከርካሪዎችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ወደ መዳረሻ ቦታዎች የሚደርሱበት የአሰራር ሥርዓት ላይ ክፍተት መኖሩንም ተጠቅሷል።

በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ መዳረሻ ቦታዎች ዕቃዎችንና ተሽከርካሪዎችን አጓጓዘው ጥቅም ላይ የዋሉ ባዶ ኮንቴነሮችን ወደ ጅቡቲ ወደብ ባለመመለሱ የኮንቴነር ክምችት መኖሩም በሪፖርቱ ተመላክቷል።


 

የኢትዮጵያ ባህር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር) እና የዘርፉ ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች የክዋኔ ኦዲት ግኝቱ ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተቋሙ ከመልቲ ሞዳል ትራንስፖርትና ከየብስ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች የነበሩበት መሆኑን ነው ኃላፊዎቹ ያብራሩት።

ይሁንና ከክዋኔ ኦዲት ግኝቱ በኋላ የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን ከመሰብሰብ ጀምሮ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ(ዶ/ር) በበኩላቸው ድርጅቱ ካለው ሀገራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አኳያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታየበትን ክፍተቶች በአፋጣኝ ማስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል።

ድርጅቱ በክዋኔ ኦዲቱ የታየበትንና የፈታበትን ሪፖርት እስከ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም ድረስ ለቋሚ ኮሚቴውና ለፌዴራል ዋና ኦዲተር አንዲያቀርብም ሰብሳቢዋ አሳስበዋል።

መልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ማለት የአንድን ሀገር የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ከመነሻ ሀገር እስከ የዕቃው መዳረሻ በአንድ ሰነድ /በባህር፣ በየብስና በአየር/ አይነቶችን ተጠቅሞ ጭነቶችን የሚያጓጉዝ የትራንስፖርት አይነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም