የኢትዮጵያ የማሪታይም ባለሥልጣን በግዥ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉበትን ክፍተቶች እንዲያርም ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

148

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን በግዥ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉበትን ክፍተቶች እንዲያርም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የማሪታይም ባለሥልጣን የ2014 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል።

የተከፋይ ሒሳብ፣ የሠራተኛ ውሰት፣ ትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ ሠራተኛ ቅጥር፣ ከግዥና ክፍያ ጋር የተገናኙ ክፍተቶች በባለሥልጣኑ ላይ የተገኙ የኦዲት ግኝቶች መካከል ናቸው።

ከግዥ ጋር በተገናኘ በ2014 በጀት ዓመት የተለያዩ ዕቃዎች ለተገዙበት የተከፈለ ከ1 ሚሊየን 400 ሺህ ብር በላይ በወጪ መያዙን የኦዲት ግኝት ሆኖ ቀርቧል።

ይህም በግዥ መመሪያ መሠረት አቅራቢዎችን በማወዳደር በግልጽ በጨረታ ግዥ መፈጸም ሲገባ በመከፋፈል በዋጋ ማቅረቢያ እንዲገዛ መደረጉን የኦዲት ሪፖርቱ አመላክቷል። 

ባለሥልጣኑ የዕቃዎችን ተፈላጊ ባህሪያት ዝርዝር ሳይጠይቅ ለመኪና ጎማ ግዥ ከ88 ሺህ ብር በላይ ክፍያ ተፈጽሞ በወጪ ተይዞ መገኘቱንም የዋና ኦዲተር ግኝት አሳይቷል። 

በተመሳሳይ ምንም ዓይነት የገበያ ጥናት ሳይደረግ በዋጋ ማቅረቢያ የግዥ ዘዴ የተለያዩ ዕቃዎች ግዥ መፈጸሙንና በዚህም ከ459 ሺህ ብር በላይ የተከፈለ መሆኑንም ሪፖርቱ ጠቅሷል።  

 ቋሚ ኮሚቴው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መመሪያን ተከትሎ ለምን ግዥ እንዳልፈጸመና የተወሰደውን የእርምት እርምጃ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቋል። 

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ ማስተካከያ የተደረገባቸውና ያልተደረገባቸው የኦዲት ግኝቶችን በኦዲት ክትትል መለየታቸውን አብራርተዋል።


 

በዚህም መሠረት አላግባብ የተከፈለ የነዳጅ ብርና የደመወዝ መጠን ጭማሪ ማስተካከያ ከተደረገባቸው ውስጥ መሆናቸውን ገልፀዋል።

እንዲያም ሆኖ ከግልጽ ጨረታ ውጪ በመከፋፈል የሚፈጸም ግዥ አሁንም መቀጠሉን ገልጸው፤ በቀጣይ መታረም እንዳለበት አሳስበዋል።

አላግባብ የተከፈለ ክፍያ፣ ከግዥ፣ ተሰብሳቢ ሒሳብና ተከፋይ ሒሳብ፣ በንብረት አስተዳደር መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ትኩረት ይፈልጋሉ ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ፤ የድርጊት መርሃ-ግብር በማውጣት ለኦዲት ግኝቶቹ ምላሽ የመስጠትና ችግሩን የፈጠሩትን አካላት ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ከተከፋይ ሂሳብ፣ ከሠራተኛ ውሰት፣ ትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ ሠራተኛ ቅጥር፣ ከግዥ፣ ከክፍያና ሌሎች የኦዲት ግኝቶች ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር የሺመቤት ደምሴ፤ የማዕቀፍ ግዥ ሲዘገይ ተቋማት በራሳቸው እንዲፈጽሙ እንደሚፈቀድ አውስተዋል።


 

ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑ ይህንን አሠራር መቀጠሉ አግባብ ባለመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግ አሳስበዋል።

ባለሥልጣኑ ከሠራተኛ ውሰት ጋር በተገናኘ የቀረበው የኦዲት ሪፖርት ላይም በአዋጁ መሠረት ማስተካከያ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል።

ሰብሳቢዋ ከግዥ፣ ከተሰብሳቢና ተከፋይ ሒሳብና ሌሎች ላይ በዋና ኦዲተር ግኝት መሠረት መፍትሔ የተወሰደባቸውና ያልተወሰደባቸውን ለይቶ እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ለቋሚ ኮሚቴውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲያሳውቅ አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም