የሳተላይት መረጃዎችን ለተቋማት ተደራሽ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እንዲጎለብቱ በትኩረት እየተሰራ ነው

429

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የሳተላይት መረጃዎችን ለተቋማት ተደራሽ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እንዲጎለብቱ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት በጂኦ-ስፓሻል ዘርፍ መረጃ ለተቋማት ተደራሽ ማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።


 

የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቤተልሔም ንጉሴ፤ ኢንስቲትዩቱ ለአምስት ዓመታት የሳተላይት መረጃዎችን ለማግኘት ከቻይና የተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ጋር ሥምምነት አድርጓል ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የሦስት ሳተላይቶች መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ወደ መረጃ ቋት እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ እነዚህን መረጃዎች በመጠቀም የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ኢንጂነር ቤተልሄም ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ለሌሎች ተቋማት የሳተላይት መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እንዲጎለብቱና የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በኢንስቲትዩቱ የሪሞት ሴንሲንግ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ብርሃን ገሠሠ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሳተላይት መረጃዎችን ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና ተያያዥ ሥራዎች መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል።


 

ለአብነትም የሰብል ምርትን ለማሳደግ፣ የእንስሳት ልማትን ለማጠናከርና የተፈጥሮ አደጋዎችን የመከላከል ተግባራትን ለማከናወን የሳተላይት መረጃዎች ወሳኝ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

በመሆኑም ተቋማት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ሥምምነት በመፈጸም የሳተላይት መረጃዎች ማግኘት እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ባነሱት ኃሳብም ኢንስቲትዩቱ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም በዘርፉ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን ለማከናወን ማቀዱ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

ከውይይቱ ጎን ለጎን የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በመረጃ ልውውጥ ሂደት በጋራ መሥራት የሚስችላቸውን ሥምምነት ተፈራርመዋል።

የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ፤ ሁለቱ ተቋማት በተናጠል ከሚሰሩት ሥራ ጎን ለጎን በትብብር ለመሥራት መስማማታቸው መረጃዎች ወቅታቸውን ጠብቀው ተደራሽ እንዲሆኑና ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ያስችላቸዋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ በበኩላቸው፤ የተሻለ ጥራት ያለው፣ ወቅታዊና ለሀገር ዕድገት ግብዓት ሊሆን የሚችል መረጃ ለማቅረብ ሥምምነቱ አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት በጂኦ-ስፓሻል ዘርፍ ያለውን ቴክኖሎጂና ዕውቀት ሳይንሳዊና ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ በማድረግ ምርትና አገልግሎቶቹን በብቃትና በጥራት በማልማት ለተለያዩ የልማት ዘርፎች ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም