አዲስ የተዘጋጀው የሕጋዊ ሥነ-ልክ አዋጅ በምርቶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር ለማጠናከር ያስችላል

154

 አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የሕጋዊ ሥነ-ልክ ረቂቅ አዋጅ በምርቶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በማጠናከር የሸማቾችን መብት ለማስከበር እንደሚያስችል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

 የሕጋዊ ሥነ-ልክ ረቂቅ አዋጅ ከንግድ ልውውጥ፣ ከጤና፣ ከደኅንነትና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ አገልግሎት ላይ የሚውሉ ልኬቶችንና የመለኪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጓል።   

የሰውንና የእንስሳትን ጤንነትና ደኅንነት ማስጠበቅ እንዲሁም የአካባቢ ብክለትን መከላከል ከዓለም አቀፍ የሕጋዊ ሥነ-ልክ ሕግጋት ጋር የተጣጣመ ሕግ በማውጣት ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስርን ማጎልበትም የረቂቅ አዋጁ ሌላኛው ዓላማ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ግብዓት በማከል ባለፈው ሐሙስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ውሳኔ አሳልፏል።

በሚኒስቴሩ የሕጋዊ ሥነ-ልክና የቴክኒክ ደንብ ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጌታቸው ወለል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ የተላከው ረቂቅ አዋጅ ለዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል። 

በተለይም ደግሞ በምርቶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በማጠናከርና ትክክለኝነትን በማረጋገጥ የሸማቾችን መብት ለማስከበር እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ እስካሁን በልኬት፣ በመለኪያ መሣሪያዎችና በታሸጉ ምርቶች ላይ የተገኙ ጉድለቶችን በሸማቾች ጥበቃና የንግድና ምዝገባ አዋጆችን መሠረት በማድረግ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል።  

ይህም ሆኖ አሁን የተዘጋጀው አዋጁ ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የንግድ ሥርዓቱን ይበልጥ ለመቆጣጠርና ጉድለቶች ሲገኙ ቀጥታ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችለው ነው ማብራሪያ የሰጡት።

ረቂቅ አዋጁ ከዓለም አቀፍ የሕጋዊ ሥነ-ልክ ሕግጋት ጋር የተጣጣመ ሕግ በማውጣት ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስርን ለማጎልበት እንደሚያስችልም ተናግረዋል። 

የሕጋዊ ሥነ-ልክ አዋጅ ፀድቆ ሥራ ላይ ሲውል በአነስተኛ ክፍያ ሲሰጥ የነበረው የአገልግሎት ክፍያ ወጪውን መሸፈን የሚያስችለው የክፍያ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ማዘጋጀቱንም ገልፀዋል።

ይህንንም ተከትሎ የንግዱ ማኅበረሰብ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለሚያገኙት አገልግሎት በቀላሉ ጊዜያቸውን ሳያባክኑ በአነስተኛ ወጪ የኦንላይን ክፍያ የሚያካሄዱበትን አሠራር እየዘረጋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ሕብረተሰቡም በልኬት፣ በመለኪያ መሣሪያዎችና በሚገዛቸው በታሸጉ ምርቶች ላይ በሚያጋጥመው ጉድለት መብቱን እንዲጠይቅና ለሚኒስቴሩ ጥቆማ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። 

ኢትዮጵያ በሕጋዊ ሥነ-ልክ የዓለም አቀፉ የሥነ-ልክ ድርጅት ሙሉ አባል መሆኗን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ከተቋሙ የቴክኒክ ድጋፍ እያገኘች መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ የሕግ ተጠያቂነትን በሚያስከትሉ በጤና፣ በደኅንነት፣ በአካባቢና የሸማቾች ጥቅም ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ልኬቶች፣ የመለኪያ መሣሪያዎችና የታሸጉ ምርቶች ላይ ቁጥጥር እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ስምንት ወራትም ክትትል ከተደረገባቸው ከ3 ሺህ 400 በላይ የመለኪያ መሣሪያዎች በ12ቱ ላይ ጉድለት በመታየቱ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

20 አምራች ድርጅቶችም ምርቶቻቸው በአብዛኛው የተቀመጠውን የደረጃ መስፈርት የማያሟሉ ሆነው በመገኘታቸው አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለውሳኔ መቅረቡንም ጠቅሷል።

በገበያ ላይ ምርታቸው ከታዩት ሦስት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአንዱ ላይ ጉልህ ጉድለት በመታየቱ እንዲታሸግ መወሰኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም