የአፍሪካ ሕብረት ከተርክዬ መንግስት ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ ይቀጥላል-  አምባሳደር ፋታላህ ሲልማሲ

192

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ሕብረት ከተርክዬ መንግስት ጋር ያለውን አጋርነትና ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአፍሪካ ሕብረቱ ኮሚሽን ዳይሬክተር አምባሳደር ፋታላህ ሲልማሲ ገለጹ።

የተርክዬ የልማት ትብብርና ኮርፖሬሽን ኤጀንሲ (ቲካ) ለአፍሪካ ሕብረት የሕብረቱን፣ የአባል አገራትን፣ የቀጣናዊ ትብብር እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ሰንደቅ ዓላማ በድጋፍ አበርክቷል።

ድጋፉንም በኢትዮጵያ ከተርክዬ አምባሳደር በርክ ባራን ለአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዳይሬክተር አምባሳደር ፋታላህ ሲልማሲ አበርክተዋል።


 

አምባሳደር ፋታላህ ሲልማሲ በዚሁ ጊዜ፤ በአፍሪካ ህብረትና በተርክዬ መንግስት መካከል በዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲና የልማት መስኮች ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ትብብር መኖሩን ገልጸዋል።

የተርክዬ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታዬፕ ኤርዶዋን እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አመራሮች እያከናወኑት ያለው  የዲፕሎማሲ ስራ ትብብሩ ይበልጥ እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ህብረቱ ከተርክዬ መንግስት ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት፡፡

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን፤ እ.አ.አ ከ2008 ጀምሮ በተርክዬና በአፍሪካ ሕብረት መካከል ያለው ስትራቴጂክ አጋርነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።


 

ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታዬፕ ኤርዶዋንም በ31 የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝነት ተርክዬ ለአህጉሪቷ ያላትን ጠንካራ አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተርክዬ በአህጉሪቷ የሚኖራትን የልማት ትብብር ለማጠናከር ሶስት ታላላቅ የተርክዬ-አፍሪካ የልማት ትብብር መድረኮችን አዘጋጅታ በስኬት ማስተናገዷን አስታውሰዋል።

የተርክዬ መንግስት ከአፍሪካ አገራት ጋር በተለያዩ የትብብር መስኮች የሚያከናወነው የልማት ሥራ የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

በትምህርትና ስልጠናም የተርክዬ መንግስት ለበርካታ አፍሪካዊያን የነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት  ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የተርክዬ አየር መንገድም የተርክዬ-አፍሪካን ንግድና ኢንቨስትመንት በማሳለጥ  አይነተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በሰንደቅ ዓላማ ድጋፍ የርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ የተርክዬ ኤምባሲ እና የተርክዬ ትብብርና ኮርፖሬሽን ኤጀንሲ (ቲካ) የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም