በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል - የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

64

ሶዶ፣ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን  የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመላከቱት በክልሉ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በተቀናጀ መንገድ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል።

 በተለይም በትምህርት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በኢንቨስትመንት ማስፋፋትና በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ዘርፍ የተሻሉ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋለውን የመፅሐፍ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ በክልሉ "አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ" በሚል ሀሳብ እየተከናወነ በሚገኘው የህዝብ ንቅናቄ የተሻለ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚሁ ሀብት የማሰባሰብ ሂደት ተስፋ ሰጪ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው ይህም ለ2017  ዓ.ም የትምህርት ዘመን በቂ መፅሐፍት ለተማሪዎች ለማሰራጨት ያስችላል ብለዋል።

በክልሉ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ገቢን አሟጦ መሰብሰብ  ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው  በበጀት ዓመቱ 75 በመቶ የሚሆነውን በጀት በውስጥ አቅም ለመሸፈን ግብ ተይዞ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።

ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የግንዛቤ ችግሮችን ለመቅረፍ ለደረጃ "ሀ" እና "ለ" ግብር ከፋዮች የሂሳብ አያያዝና ደረሰኝ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ  ስልጠና በመሰጠቱ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ባለፉት ዘጠኝ  ወራት በተደረገው ጥረትም ከ11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 183 ባለሀብቶች  የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውሰጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ባለሀብቶቹ ከተሰማሩባቸው መስኮች መካከል ግብርና፣ በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዋንኞቹ መሆናቸውን ወይዘሮ ሰናይት አስታውቀዋል።

በቀጣይም ዘርፉን ይበልጥ ለማነቃቃትና ያሉትን ማነቆዎች በመፍታት ተገቢውን ውጤት ለማስመዝገብ በክልሉ የኢንቨስትመንት ፎረም ለማዘጋጀት መታቀዱንም አብራርተዋል።

በክልሉ እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍና የአፈር ናዳ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ከወዲሁ ከክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር  ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህ ረገድ በክልሉ ጌዴኦ፣ ወላይታ፣ አሪ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ አሌ፣ ባስኬቶና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ስር የሚገኙ 148 የአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቀበሌዎችን  በመለየት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መጀመራቸውን አመልክተዋል።

እንደ ወይዘሮ ሰናይት ገለፃ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ቀሪ ጊዜያት በክልሉ መንግሥት አቅጣጫ እንዲሁም በፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን ግብረ መልስ መሠረት የ100 ቀናት እቅድ ተዘጋጅቶ ርብርብ  እየተደረገ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም