በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገር  ዕድገት ላይ የሚያበረክቱትን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ተጠየቀ

64

ድሬዳዋ ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ዕድገትና ልማት ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ  ለማሳደግ  አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የንግድና ኢንቨስትመንት አስተባባሪ አቶ ጀማል ዑመር ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት የንግድና ኢንቨስትመንት አስተባባሪ ከድሬዳዋ አስተዳደር የአመራር አባላት ጋር "በዳያስፖራ የኢንቨስትመንትና የቤት ልማት ፓኬጅ ቀረፃ" ላይ መክሯል።

አቶ ጀማል ዑመር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ለዳያስፖራው የተቀረፀው ፓኬጅ  በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በልማትና በሀገር ዕድገት ውስጥ የሚያበረክቱትን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዝ ነው።

በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በቤቶች ልማት፣ በ'ሬሚታንስ'  እና  በንግድ ዘርፎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያለመ ነው።

ወደ ሀገር ቤት ሲመጡም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አክለዋል።

በተጨማሪም የዕውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርጉባቸውን መስኮች ለማስፋት የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎችን መልሶ በማቋቋም፣ በገበታ ለአገር፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብና ኮቪድን በመከላከል ስራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማድረግ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን የማልማት ፍላጎቱን በተግባር ማሳየቱንም አቶ ጀማል አንስተዋል።

"የተዘጋጀው ፓኬጅ እነዚህን ተግባራት ይበልጥ ለማሳደግ፣ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንትና የንግድ ተሳትፎውን ለማጎልበትና በተለያዩ አማራጮች የቤት ባለቤት ለማድረግ ያለመ ነው" ብለዋል።


 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  በልማትና በኢንቨስትመንት ላይ እያበረከቱ የሚገኙት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በተለይም በድሬዳዋ ባለፉት ሁለት ዓመታት  "ናፍቆት-የድሬዳዋ ሳምንት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጁት መድረኮች በመላው ዓለም የሚገኙት የአካባቢው ተወላጆችና ወዳጆች ተሳትፎና ትስስር መጠናከሩን አስታውሰዋል።

እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም የዳያስፖራ ማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ከአገር አቀፉ ፓኬጅ የተቀዳ በድሬዳዋ ተጨባጭ ሁኔታ የዳያስፖራ ፓኬጅ  ተዘጋጅቶ በቁርጠኝነት ይተገበራል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም