በመዲናዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህዝብን በማሳተፍ ውጤታማ የሰላም ግንባታ ስራ ተከናውኗል-የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ

418

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡-በመዲናዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህዝብን በማሳተፍ ውጤታማ የሰላም ግንባታ ስራ መከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የከተማዋ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸማቸውን በዛሬው እለት ገምግመዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ወቅት፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የዓለም 3ኛዋ የዲፕሎማቲክ ማዕከል እና ግዙፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑባት ከተማ  መሆኗን ተናግረዋል፡፡ 

በመሆኑም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዘመናዊ፣ የተቀናጀ እና የተደራጀ የሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ስራ መከናወኑን አውስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ስፊ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በከተማዋ አሁን ላይ ከ141 ሺህ በላይ የሰላም ሰራዊት አባላት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሰላም ሰራዊት አባላቱ ከከተማዋ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ወንጀልን መከላከልና የከተማዋን ሰላም የማስጠበቅ ስራዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም በመዲናዋ የወንጀልና የደንብ መተላለፍ ድርጊቶችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመከላከል ረገድ በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ህዝብን ያሳተፈ ወንጀል መከላከል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘርይሁን ተፈራ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና የጎዳና ላይ ንግድ መከላከልን ጨምሮ የተሻለ የደንብ ማስከበር ስራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡


 

በከተማ አስተዳደሩ መሬት ባንክ የሚገኙ መሬቶች ላይ ህገ ወጥ ወረራ እንዳይፈጸም በመከላከል ረገድም ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ነው ያሉት፡፡

በበርካታ ቁማር ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች፣ ጫት ቤቶችና ሌሎች የማህበረሰቡን ሰላም በሚያውኩ ስፍራዎች ላይ የተቀናጀ  ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ነው ያነሱት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም