የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅምን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ እየተሰራ ነው 

239

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡-የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ  ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ። 

የ2016 ኢትዮጵያ ታምርት 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በመጪው ሚያዝያ 13 በአዲስ አበባ  እንደሚካሄድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሩጫው በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን መነሻና መድረሻው መስቀል አደባባይ መሆኑ ተጠቅሷል። 

ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ ኢትዮጵያ ታምርት የሩጫ ውድድር ከ22 ክለቦች የተውጣጡ አትሌቶች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ይሳተፋሉ ተብሏል።  

በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑት ከ50 ሺህ እስከ 250 ሺህ ብር ሽልማት እንደተዘጋጀም ተጠቁሟል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ሩጫውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ የሩጫ ውድድሩ የሚካሄደው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ነው። 

በተለይም በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ የስፖርት ትጥቆችን ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና በዘርፉ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ውድድሩ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች  ከስፖርቱ ጋር  በማስተሳሰር አምራቹ የሰው ኃይል ጤንነቱ ተጠብቆ የማምረት አቅሙን ለማጎልበት ታስቦ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል። 

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ለማስተዋወቅና የመጠቀም ባህልን ለማሳደግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም የአገር ውስጥ ምርቶችን በሰፊው በማምረትና የመጠቀም ባህልን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ  ምርቶችን በእጅጉ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሥር ዓመት የልማት መሪ ዕቅድ ስትራቴጂክ የሆኑ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶችን በማስፋፋት የአገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶችን ጠቅላላ የአገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም