ኮርፖሬሽኑ ከጀርመን ኩባንያ ጋር የ1.2 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ 

174

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡-የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከጀርመን የስራ እድል ፈጠራ ማስተባበሪያ ቢሮ  ( The Facility Investing for Employment ( IFE ) ጋር የ1.2 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራርሟል። 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ማስተባበሪያ ቢሮው የስራ እድል ፈጠራን መጨመር፤ የውሀ አቅርቦት ተደራሽነትን ለማሳደግ እንዲሁም የአምራች ኩባንያዎች አቅም ማሳደግና እርካታን ለመጨመር በመተባበር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አድንቀዋል። 



ኮርፖሬሽኑም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ግዜ ተጠናቆ በሙሉ አቅም ተግባራዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስ አረጋግጠዋል። 


 

ስምምነቱ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የንፁህ ውሀ አቅርቦትን ለማሳደግ፤ የአምራች ኩባንያዎችን እርካታ በመጨመር ፓርኩ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ እና ከ300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ያለመ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ነውም ተብሏል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሐይለሚካኤል፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እንዲሁም የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና እድገት ሚኒስትር ማስተባበሪያ ዶ/ር ዶሚኒካ ፕሪይዚንግን ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም