ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳትና አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል -የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

497

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳትና አስተሳሰብ መያዝ እንደሚያስፈልግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት “ሀገራዊ መግባባት እና የኮሙኒኬሽን ተቋማት ሚና” በሚል ርእስ ለኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡


 

በሥልጠና መርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳትና አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመሠረታቸዉ በመረዳት የሰላም ግንባታ ሂደቱን ለማፋጠን የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሚና ከፍ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ተቋማት፣ ከዞንና ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ከየፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ነው፡፡ 


 

በሥልጠናዉ የመጀመሪያ ቀን ውሎው “የገዥ ትርክት ግንባታ እና የኮሙኒኬሽን ሚና” በሚል ርእስ የዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ ገለጻ አቅርበዋል፡፡ 

ገዥ ትርክት የሀገር አንድነት መሠረት መሆኑን ያመላከቱት አቶ አዲሱ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ትርክቱን በመትከልና በማጽናት ጉልህ ሚና እንዳለዉ አስገንዝበዋል፡፡

ቀድሞ ተንባይ የኮሙኒኬሽን ሥርዐት በመከተል ገዥ ትርክትን መገንባት ላይ ሰፊ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሥልጠናው ዓላማ የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉን በሥልጠና በማገዝ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ፣ የተናበበ እና የተቀናጀ መረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥና ሚዲያን በአጀንዳ ለመምራት ዐቅም ለመፍጠር ነውም ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂ በመረዳት የሀገረ መንግሥት ግንባታውን በኮሙኒኬሽን ለመደገፍ፣ ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ በፍጥነትና በጥራት ለመስጠት እንደሚጠቅማቸዉ ገልጸዋል፡፡

ተመሳሳይ ይዘትና ዓላማ ያለዉ ሥልጠና ከዚህ ቀደም ለሕዝብ እና የንግድ መገናኛ ብዙኃን አመራሮችና ባለሙያዎች መሰጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

በዛሬዉ ሥልጠና ደግሞ እስከ 200 የሚደርሱ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡ 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በትኩረት እየሠራባቸዉ ካሉ ጉዳዮች መካከል የዘርፉን የሰው ኃይል ዐቅም መገንባት አንዱ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም