የማቲዎስ ወንዱ የካንሰር ሶሳይቲ ባለፉት 20 ዓመታት ከ 3 ሺህ በላይ የካንሰር ህመምተኞችን አግዟል

234

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የማቲዎስ ወንዱ የካንሰር ሶሳይቲ ባለፉት 20 ዓመታት  ከ 3 ሺህ በላይ የካንሰር ህመምተኞችን ማገዙን አስታወቀ።

 ሶሳይቲው የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት በተለያዩ መርኃ ግብሮች አክብሯል።

በበዓሉ ላይ የማህበሩ አባላት፣ የማህበሩ ተጠቃሚዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የማቲዎስ ወንዱ - የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንዱ በቀለ በመስክረም 1996 ዓ.ም የአራት ዓመት ልጃቸውን ማቲዎስ ወንዱን በደም ካንሰር በሽታ ማጣታቸውን ተከትሎ ማህበሩን መመስረታቸውን ተናግረዋል።

ልጃቸውን በካንሰር ህመም ቢያጡም ሌሎች ልጆችን ከዚህ ህመም መታደግ እንችላለን በሚል መሪ ሀሳብ ልጃቸውን ባጡበት ዓመት በሚያዚያ 1996 ዓ.ም ሶሳይቲው መመስረቱን ገልጸዋል።

ሶሳይቲው አሁን ላይ የካንሰር ታማሚዎችን በመደገፍ 20 ዓመታትን ማስቆጠሩን ገልጸዋል።

ማህበሩ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት አቅም የሌላቸው የካንሰር ህመምተኞች የህክምና ወጪያቸውን የሚሸፍኑበትን ድጋፍ መስጠት ላይ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሰዎች ስለካንሰር ህመም እና ሌሎች ተላላፊ ስላልሆኑ በሽታዎች በቂ ግንዛቤ በመያዝ ጤናቸውን እንዲጠብቁ የሚያግዝ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን  ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው አፈጻጸም ሶሳይቲው ከ 3 ሺህ በላይ የካንሰር ህመምተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን መርዳት መቻሉን አንስተዋል።


 

በአሁኑ ሰዓት ማህበሩ ከ170 በላይ የካንሰር ህሙማን ህክምናቸውን በተገቢው መንገድ እንዲከታተሉ ለአስታማሚዎቻቸው እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የካንሰር ህመም የተገኘባቸውን ልጆቻቸውን ለማሳከም አዲስ አበባ የመጡና በበዓሉ ላይ የታደሙ ወላጆች ሶሳይቲው እያደረገላቸው ለሚገኘው ድጋፍ ከልብ አመስግነዋል።

በተለይም ሶሳይቲው ባመቻቸው ማረፊያ ቆይታቸውን በማድረግ ልጆቻቸው ያለምንም መጉላላት የህክምና ክትትላቸውን  እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሶሳይቲው ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን የህክምና ወጪ በመሸፈን ረገድ የሚያደርግላቸው እገዛ ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም