በሀገሪቱ ክህሎት መር  የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋፋት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል--ሚኒስቴሩ

127

ሚዛን አማን፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ) ፡- በሀገሪቱ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋፋት የዜጎችን ዘላቂ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከቤንች ሸኮ ዞን ከተውጣጡ የሥራ ዕድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ባለድርሻ አካላት ጋር በሚዛን አማን ከተማ እየመከረ ነው።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰሎሞን ሶካ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፣ አዳዲስ እሳቤዎችን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።

ለዚህ እውን መሆን የሥራ ዕድል ፈጠራው በክህሎት መመራት እንዳለበት ጠቁመው፣ በሚኒስቴሩ በኩል ይህንን ታሳቢ ያደረገ የለውጥ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የለውጥ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እኩል ግንዛቤ ኖሯቸው ዘርፉን መምራት እንዲችሉ ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክልሎች ስልጠና ነክ ምክክሮች በመደረግ ላይ ናቸው ያሉት አቶ ሰለሞን፣ በቤንች ሸኮ ዞን ካሉ የሥራ ዕድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ባለድርሻ አካላት ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት አካባቢው ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን እምቅ አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ክልሉ ያለው የተፈጥሮ ፀጋ ለዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህን ሀብት በአግባቡ አስተዳድሮ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሀገር ደረጃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማጠናከር በየክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀምና ለወጣቱ ክህሎትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፣ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ጥረት የወጣቱ ድርሻ እንዲጎላ ወጣቱን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ፍላጎትን መሰረት ባደረጉ የሥራ ዘርፎች ማሰማራት ያስፈልጋል። 

የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር አስተሳስሮ በማስኬድ በዘርፍ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት በርብርብ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ጋኪያብ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቷል።  

የክልሉ መንግስት የዜጎችን በተለይም የወጣቶችን የሥራ ዕድል ጥያቄዎች ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለ44 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የሥራ ዕድል ለሚፈጠርላቸው ወጣቶች በሚሠሩት ሥራ ክህሎታቸውን ለማዳበር የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንና ይህም የሥራ ዕድል ፈጠራው ክህሎት መር እንዲሆን እያገዘ ነው ብለዋል።

በክልሉ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተያዘውን ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ እንዲሳካ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉም አቶ ግዛው አስገንዝበዋል።

በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በቤንች ሸኮ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተቋማትን የሚመሩ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም