150 ኢትዮጵያውያን እና የአሜሪካ ባለሃብቶች የተሳተፉበት የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተካሄደ

177

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- 150 ኢትዮጵያውያን እና የአሜሪካ ባለሀብቶች የተሳተፉበት የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተካሂዷል።

ጉባኤው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ዋፋ ማርኬቲንግ ኤንድ ፕሮሞሽን በትብብር የተዘጋጀ ሲሆን  በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የሚመራ ልኡክ ተሳትፎበታል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) እንዳሉት ጉባኤው በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመለየትና በዚህም ዙሪያ ለመወያየት እድል ፈጥሯል ብለዋል።

ጉባኤው በኢንቨስተሮች መካከል ትስስር ለመፍጠር የሚያግዝ መድረክ መሆኑንም አምባሳደር ስለሺ ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ሀገራት በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አክለው ይህም ሀገሪቱን ዋና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ያደርጋታል ብለዋል።

በተጨማሪም በቅርቡ እንደ ጎግል፣ሜታ፣ዳታበሪክስ እና ፕላንቲር ከመሳሰሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር የተደረጉ ትብብሮች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ያሳየ ነው ብለዋል።

በአቪዬሽን፣ በአይቲ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና የሰው ሃይል ልማት እንደጨርቃጨርቅ፣ ማዕድን፣ ፋይናንስ እና ቴሌኮም ባሉ ዘርፎች የተመዘገቡ አበረታች እድገቶች ሀገሪቱን ቀዳሚ የኢንቨስተትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት አምባሳደር ስለሺ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም