ኢትዮጵያ በ60ኛው ዓለም አቀፍ የአርት ኤግዚቢሽን እየተሳተፈች ነው

179

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በቬኒስ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 60ኛው ዓለም አቀፍ የአርት ኤግዚቢሽን የሀገሪቱን ልዩ ልዩ ሀብቶች በሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች እየተሳተፈች ትገኛለች።

በጣሊያን ሀገር በቬኒስ ከተማ 60ኛው ዓለም አቀፍ የአርት ኤግዚቢሽን በዛሬው እለት ተከፍቷል። 

በኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ባህላዊና የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ በታዋቂው ኢትዮጵያዊው አርቲስት ተስፋዬ ኡርጌሳ የአርት ስራዎች የቀረቡበትን የኢትዮጵያ ፓቪሎን በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ተመርቆ ተከፍቷል።  

በፓቪሎኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመደመር መጽሐፍ ለዝግጅቱ ታዳሚያን በማቅረብ በብልጽግና የመደመር መሰረታዊ እሳቤዎች ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያዝ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


 

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቡና አፈላል ስነ-ስርዓት እና ሌሎች የሀገራችንን ባህላዊ እሴቶች የሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች ለታዳሚው ቀርበዋል። 

የኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያ ኮሚሽነር የሆኑት በጣሊያን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ቱሪዝም በሀገራችን ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በዘርፉ የተከናወኑ አበረታች ስራዎችን ለታዳሚያኑ አቅርበዋል።

አያይዘውም አገራችን በጥበብ ስራዎችና በቱሪዝም ሀብት ያላትን የካበተ አቅም እና ከሌሎች የተለየ የሚያደርጋትን በመግለጽ ታዳሚዎች አገራችንን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኤግዚቢሽኑ በዓለም ከሚካሄዱ መሰል ዝግጅቶች መካከል ልዩ ትኩረት የሚሰጠውና ለስድስት ወራት የሚቆይ መሆኑም ተመልክቷል።

በዚህም የኢትዮጵያን የጥበብ ስራዎች፣ የቱሪዝም ሀብቶች እንዲሁም ባህላዊ እሴቶቻችንን በመድረኩ በሰፊው በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን ከፍታ በዓለም ዙሪያ በበቂ ሁኔታ ለማሳየት እድል የፈጠረ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም