በሐረሪ ማህበረሰብ የሙዚቃ ቅኝት ዙሪያ ተጠንቶ  የተዘጋጀ  መጽሃፍ ተመረቀ

116

ሐረር ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡-  በሐረሪ ማህበረሰብ ቱባ የዜማ ባህልና የሙዚቃ ቅኝት ዙሪያ ተጠንቶ የተዘጋጀ መጽሃፍ ዛሬ ለምረቃ በቃ።

በአዲስ አበባ ባህል፣ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አማካኝነት የተዘጋጀውን መጽሃፍ የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሃት ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አፈ ጉባዔ አቶ ሙህየዲን አህመድ በማስረከብ በይፋ ተመርቋል።

መጽሃፉ በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን ፤ በውስጡም የጥናቱ ዳራ፣የተዛማጅ ዕሁፍ ቅኝት፣የዜማ ስልተ ምትና ቅኝት ጽንሰ ሃሳብ፣የጥናት አካባቢ መግለጫና የአጠናን ዘዴ፣የመረጃ ትንተና፣ትርጉም እና ግኝትን የያዘ መሆኑን በስነ- ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። 

መጽሃፉም የሐረሪ ብሔረሰብ በኢትዮዽያ ውስጥ እንዳሉት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ ተዝቆ  የማያልቅ ቱባ የስልተ ምት እንዲሁም ማህበራዊ ክንዋኔ ባለቤት እንደመሆኑ ይህንኑ የሀገር ሃብት ከምንጩ በማጥናት ማስተዋወቅና መሰነድ ዓላማ ያደረገ እንደሆነም ተመልክቷል።

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አፈ ጉባዔ አቶ ሙህየዲን አህመድ እንደገለጹት፤ ሐረር የጥበብ ሰዎች መፍለቂያ ብቻ ሳትሆን የበርካታ ጥበብ ባለቤትም ጭምር ናት።

ከነዚህም ጥበቦች መካከል የሐረሪ ሙዚቃ አንዱ እና ልዩ የሆነ የኪነ ጥበብ ሐብቷ ለዘመናት በተለያዩ መጠን ና ይዘቶች ጥናት ለማድረግ ቢሞከርም አመርቂ ውጤት ሳይገኝበት ቀርቷል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ  ይህንን ጥናት በአጭር ጊዜ አጥንቶ እንዲሁም በመጽሐፍ አትሞ ለንባብ ማብቃቱ ዳግም የሐረሪ ሙዚቃ እንዲያናሰራራ እና እንዲተዋወቅ ከማድረጉም በተጨማሪ ለቀጣይ ጥናቶች በር የከፈተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሀላፊ  አቶ ሰርፀ  ፍሬስብሀት ፤ የሐረሪ ህዝብ ከ1 ሺህ ዓመት በላይ ታሪክና ቅርስን ይዞ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።

የሐረሪ ሙዚቃ ልዩ ስልተ ምት ያለውና ከሀገራችን ሌሎች ሙዚቃዎች ጋር ያለው አንድነትና ልዩነትን የሚያሳይ ሰፊ ጥናት ሊካሄድበት የሚገባና በጥናት ለመፈተሽ የሚስብ ኪነ ጥበብ ነው ሲሉ  አንስተዋል።

ይህን መሰረት በማድረግ የአዲስአበባ ባህልና ኪነጥበብ ቢሮ ከክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የሐረሪ ሙዚቃ ላይ ያተኮረ ጥናት መካሄዱን አስረድተዋል።

በምረቃው ስነ ስርዓት የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም