በክልሉ  ወርቅ አመራረት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ የንቅናቄ መድረክ  በአሶሳ እየተካሄደ ነው 

87

አሶሳ ፤ ሚያዚያ  9/2016 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅ አመራረት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ የንቅናቄ መድረክ  በአሶሳ ከተማ  እየተካሄደ ነው።

የንቅናቄ መድረኩ እየተካሄደ ያለው “የማዕድን ሀብታችን ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በዚህ ወቅት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን እንደገለጹት፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበረው የማዕድን ዘርፍ ጣልቃ ገብነት  መወገዱን ተናግረዋል፡፡

የማዕድን ሀብት የማይታደስ እና አላቂ ሃብት እንደሆነ አመልክተው፤ አጠቃቀማችን ህገወጥነትን የተከላከለና የህዝባችን ዘላቂ ህይወት በመቀየር ሃብቱ በአግባቡ ለትውልድ የሚሸጋገር ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህም በየደረጃው የሚገኝ አመራር፣ በማዕድን ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች እና ባለድርሻ አካላት ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም ህገወጥነትን አጥብቀው መከላከል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡


 

በንቅናቄው ማስጀመሪያ መድረክ ላይ የተገኙት የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው፤ ያደጉ ሀገራት ከድህነት የወጡበት  የተፈጥሮ ሃብታቸውን በሚገባ በማልማታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

የማዕድን በሚገባ መልማት እንዱስትሪውን እና ግብርናውን ማዘመን ከማስቻሉ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ በማሳደግ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ኢኮኖሚውን መቀየር እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያም ከሃገራዊ ለውጡ በኋላ በተለይም የማዕድን ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ተሻሽለው ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ አዋጆችን እና ፖሊሲዎች በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት ከለያቸው አምስት የሀገሪቷ የኢኮኖሚ አውታሮች ውስጥ የማዕድን ዘርፍ አንዱ ነው ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከዋነኞቹ የወርቅ ሀብት መገኛ ከሆኑ የሀገሪቱ  ክልሎች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቁመው ፤ በክልሉም ሆነ በመላ ሀገሪቷ ባለው አቅም ልክ አለመመረቱን አንስተዋል።

የንቅናቄው መድረከ በቀጣይ ሁለት ዓመታት በወርቅ ሀብት አመራረት ረገድ መሠረታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ የሚያግዝ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡


 

በቅርቡ ከሚተገበሩ ስራዎች መካከል ደግሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ በዓመት ከዘጠኝ ቶን በላይ ወርቅ ማምረት የሚያስችል ዘመናዊ የወርቅ ኩባንያ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ተግባራዊ ስራ እንደሚጀምር አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በመተከል ዞንም በፍለጋ ላይ ያለውን የሚድሮክ ወርቅ ማምረቻ ኩባንያ በሚገባ ወደ ስራ በማስገባት ኢትዮጵያ በዓመት የምታመርተውን ወርቅ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በአንጻሩ የወርቅ ማዕድን ዘርፉ  ለህገወጥነት የተጋለጠ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሚሊዮን፤ ይህን ለማስቆም ቅንጅት፣ እውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም  በመሠረታዊነት እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ የአምራቾች ማህበራት እና ጉዳዩ የሚመከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም