የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዞን ለማፋጠን የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄን በመተግበር አበረታች ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው 

118

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዞ ለማፋጠን የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄን በመተግበር አበረታች ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

አቶ መላኩ አለበል ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች ፈጠራ እና ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጉንተር በገር ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይታቸው በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ በማተኮር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሀገር አቀፍ አጋርነት(PCP) ፕሮግራም አተገባበር፣ ዘላቂ የልማት አቅምን ማሳደግ ዓላማው ያደረገ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋምና ሌሎች የጋራ ትብብር በሚያደርጉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) ጋር የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ውጤታማ በማድረግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ በማሻሻል የኢኮኖሚ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ዕውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጭ የትብብር ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። 

አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አነስተኛ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች ጥራት ያለው በርካታ የግብርና ምርት በማምረትና ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ አስተዋፅኦው የላቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ስናስብ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ እንደሚገባም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዞ ለማፋጠን የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄን ተግባራዊ በማድረግ አበረታች ስኬቶች እየተመዘገቡ ነውም ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) እያደረገ ላለው ድጋፍ ሚኒስትሩ አመስግነው ለንቅናቄው ዓላማ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች ፈጠራ እና ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጉንተር በገር በበኩላቸው ለሀገር አቀፍ አጋርነት(PCP) ፕሮግራም አተገባበር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ዘላቂ የልማት አቅምን ማሳደግ ዓላማው ያደረገ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም የተደረሰው ስምምነት ፍሬ እንዲያፈራ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩ መግለጻቸውም በመረጃው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም