ማዕከሉ በምርምር ያገኛቸውን የሽምብራና የጤፍ ምርጥ ዘሮች እንዲለቀቁ ማድረጉን ገለፀ

238

አክሱም፤ ሚያዝያ 9/2016(ኢዜአ)፡- የአክሱም እርሻ ምርምር ማአከል በምርምር ያገኛቸውና በምርታማነታቸው የተሻሉ የሽምብራና የጤፍ ዝርያዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲለቀቁ ማድረጉን አስታወቀ።

በምርምር የተገኙት ሁለቱም ዝርያዎች በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም ከአክሱምና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች በተዋቀረ ዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ ዕውቅና አግኝተው በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲለቀቁ መደረጉን ማዕከሉ ገልጿል። 

የአክሱም እርሻ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ ፅጋቡ ንርአ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የምርምር ማዕከሉ ወደ ስራ ከገባ ወዲህ በጤፍ፣ በሽምብራና በዶሮ ላይ ምርምር እያካሄደ ይገኛል ። 

''በምርምር የተገኙት የሰብል ዝርያዎቾ በአምስት የሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎች የመስክ ምልከታ የተካሄደባቸው በመሆናቸው አሁን ወደ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገቡ ይደረጋል'' ብለዋል። 

በምርምር የተገኙት ምርጥ ዘሮች ድርቅንና ፀረ-ሰብል ተባዮችን ከመቋቋም ባለፈ በሶስት ወራት ውስጥ ለምርት እንደሚደርሱም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።  

"ሓፀቦ" የሚል ስያሜ የተሰጠው የጤፍ ዝርያ ከደብረዘይት የእርሻ ምርምር ከተገኘ ቀሚርና ሌላ የጤፍ ዓይነቶች ጋር የተዳቀለ መሆኑን አውስተዋል። 

አዲሱ ዝርያ አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት ይጠቀምበት ከነበረው የአካባቢ የጤፍ ዝርያ ከ13 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው ምርት እንደሚሰጥ የገለፁት ደግሞ በአክሱም እርሻ ምርምር ማዕከል የስነ-ማዳቀል ተመራማሪ አቶ ቸኮለ ንጉስ ናቸው። 

''በምርምር የተገኘው የጤፍ ምርጥ ዘር በሄክታር እስከ 26 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህም አርሶ አደሩ አሁን እየተጠቀመበት  ከሚገኘው ዝርያ በስምንት ኩንታል ብልጫ አለው'' ብለዋል። 

የሽምብራ ዝርያ ተመራማሪው አቶ ኪሮስ ወልዳይ በበኩላቸው በምርምር የተገኘው ሽምብራ በአካባቢው በሄክታር 18 ኩንታል የነበረውን የምርት ውጤት ወደ 27  ኩንታል ከፍ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።  

የአክሱም እርሻ ምርምር ማእከል ከዚህ ቀደም በምርምር ያገኛቸው የዳጉሳና የጤፍ ዝርያዎች እውቅና አግኝተው አርሶ አደሮች ጥቅም ላይ እንዲያውሉት ማድረጉ የሚታወስ ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም